የአዋሽ ሰባት የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የረጅም ጊዜ ጥያቄያችንን መልሶልናል-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአዋሽ ሰባት የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የረጅም ጊዜ ጥያቄያችንን መልሶልናል-ነዋሪዎች
አዋሽ ሰባት፤ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፡-በከተማው ትናንት ለአገልግሎት የበቃው የአዋሽ ሰባት የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የረጅም ጊዜ ጥያቄያችንን መልሶልናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
ወይዘሮ ከዲጋ አብዱ በሰጡት አስተያየት፤ ይህ ፕሮጀክት ዕውን በመሆኑ ቀደም ሲል ከሚደርስባቸው ወጪና እንግልት እንደታደጋቸው ተናግረዋል።
አቶ ጌትነት ኃይሉ በበኩላቸው፥የፕሮጀክቱ ሥራ መጀመር የነበረውን የውኃ ችግር መቅረፉን፤ ለውኃ ፍለጋ የሚያደርጉትን ረጅም ጉዞና የጊዜ ብክነትም ማስቀረቱን ገልጸዋል።
ለረጅም ጊዜ የቆየው የውኃ ችግራችን ተቀርፎ በየቤታችን ውኃ ማግኘት ችለናል ያሉት ደግሞ አቶ መንግሥቱ ሰፊነው ናቸው።
የዚህ ፕሮጀክት ዕውን መሆን በየደጃቸው ውኃ ማግኘት እንዲችሉ ያደረገ በመሆኑ መደሰታቸውንና የዘመናት ጥያቄያቸውን የመለሰ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአዋሽ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አብዶ ዓሊ ደግሞ፤ የለውጡ መንግሥት የከተማዋን እድገት ለማፋጠን ሕዝብን ባሳተፈ መንገድ ስኬቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክትም የሕብረተሰቡን የረጅም ጊዜ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ የፈታ ነው ብለዋል።