ቀጥታ፡

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤታማ እንዲሆን ቅንጅታዊ ሥራዎች ተከናውነዋል

ጅግጅጋ፤ ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ውጤታማ ለማድረግ  ዘርፈ ብዙ ዝግጅት መደረጉን ባለድርሻ አካላት ተናገሩ።


 

ተማሪ መሐመድ አሕመድ ለኢዜአ እንዳለው፤ መምህራን ከሚያደርጉላቸው የማጠናከሪያ ድጋፍ ጎን ለጎን ከጓደኞቹ ጋር በመሆን እያጠኑ ነው።


 

ፈተናው በበይነ መረብ የሚሰጥ በመሆኑ ከወዲሁ ቴክኖሎጂን በመለማመድ ዕውቀታቸውን ማጎልበት ላይ መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ ተማሪ ካሊድ እስማኤል ነው።


 

የሼክ አብዱሰላም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሠ መምህር አብዱልቃድር አብድራህማን እንደገለጹት፤ የግብዓት አቅርቦትና የሰው ኃይል ዐቅም ግንባታ ላይ በቅንጅት መሠራቱን አንስተው በዚህም የሀገር አቀፍ ፈተናን ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
 
በክልሉ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤቶች ማሻሻል ዳይሬክተር መሐመድ መታን በበኩላቸው፤ በ2018 ሀገር አቀፍ ፈተና ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አረጋግጠዋል።

ፈተናውን ከ16 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚወስዱ ገልጸው፤ የተማሪዎቹን  ውጤት ለማሻሻል  ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሠጣቸው መመቻቸቱን ተናግረዋል።
 
የተማሪዎቹን የትምህርት አቀባበል ለመለካት የሙከራ ፈተናዎችን በመስጠት በየጊዜው ክፍተቶችን በመለየት የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አመላክተዋል።
 
የመማሪያ መጻሕፍትን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ እንዲደርስ መደረጉንና በማጠናከሪያ ትምህርት ከ9ኛ እስከ 11ኛ ክፍል የመከለስ ሥራ መከናወኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም