ቀጥታ፡

በጭሮ ከተማ የነዳጅ አቅርቦትና አጠቃቀም መንግሥት ባስቀመጠው አሠራር መሰረት እየተተገበረ ነው

ጭሮ፤ሚያዝያ 16/2018(ኢዜአ)፦በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ የነዳጅ አቅርቦትና አጠቃቀም መንግሥት ባስቀመጠው አሠራር ብቻ እንዲከናወን እየተደረገ መሆኑን የከተማው የሥራ ዕድል ፈጠራና ንግድ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ተወካይ አቶ አደም የሱፍ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የነዳጅ ስርጭቱን ሕጋዊነት በመከታተልና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የአገልግሎት ዘርፎች በማዳረስ እጥረት እንዳይከሰት ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የነዳጅ ስርጭቱን ሕጋዊነት የማረጋገጥና በአጥፊዎች ላይ የተለያዩ የቅጣት እርምጃዎች መወሰዳቸውንም አመልክተዋል።

በሕገወጥ መንገድ ነዳጅን በማከማቸት ዋጋ ጨምረው ሲሸጡ የተገኙ በርካታ ግለሰቦች ከ30 ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ብር መቀጣታቸውንም ገልጸዋል።

በጭሮ ከተማ የነዳጅ ማደያ ባለቤት አቶ አብደላ መሐመድ በበኩላቸው፤ ከመንግሥት በወረደው አቅጣጫ መሠረት ነዳጁን በአግባቡና በቁጠባ በማሰራጨት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ባለፉት 30 ቀናት ውስጥ ከ240 ሺሕ ሊትር በላይ ነዳጅ በቁጠባና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው አካላት በአግባቡ ማሰራጨታቸውን ጠቁመዋል።

ችግሩ እስኪፈታ ድረስ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም