ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ይጀመራል 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16 /2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከ17 እና 18 ዓመት ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታዎች በኋላ ዛሬ በ22ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ይመለሳል። 

መቻል ከአዳማ ከተማ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።

መቻል በሊጉ እስከ አሁን 21 ጨዋታዎችን አድርጎ በ13ቱ አሸንፎ በሁለቱ ተሸንፎ ስድስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 38 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 12 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ቡድኑ በ45 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው አዳማ ከተማ በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 21 ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ 10 ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪው ስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 15 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያገናኝ 38 ጎሎች አስተናግዷል።

አዳማ ከተማ በ21 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። 

መቻል ከ21ኛ ሳምንት የአቻ ውጤት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

አዳማ ከተማ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ከድል ርቋል። ማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።

በሌላኛው መርሐ ግብር ሲዳማ ቡና ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሲዳማ ቡና እስከ አሁን በሊጉ 21 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን ስምንቱን ሲያሸንፍ በዘጠኙ ሽንፈት አስተናግዷል። በአራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 

በ21ዱ ጨዋታዎች ላይ 20 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 27 ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ28 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ በበኩሉ ካከናወናቸው 21 ጨዋታዎች መካከል በ12ቱ ድል ሲቀናው ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሰባት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 34 ግቦችን ሲያስቆጥር 12 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

ሃዋሳ ከተማ በ43 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያላሸነፈው ሲዳማ ቡና ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል። 

በ21ኛ ሳምንት ከሸገር ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያየው ሃዋሳ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

ሸገር ከተማ ከልደታ ክፍለ ከተማ  ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ40 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ልደታ ክፍለ ከተማ በ18 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ባለፉት ሶስት የሊጉ ጨዋታዎች አቻ የወጣው ሸገር ከተማ ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።

ልደታ ክፍለ ከተማ ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት እስከ ሚያዝያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።


 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ54 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።

የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞን በ22 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራች ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ረድኤት አስረሳኸኝ በ16 ጎሎች ትከተላለች።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም