ቀጥታ፡

በጅማ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 52 ሺህ ቶን ቡና ለገበያ ቀርቧል  

ጅማ፤ ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፡- በጅማ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 52 ሺህ ቶን ቡና ለገበያ መቅረቡን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቲጃኒ ተማም ተናገሩ።

ኃላፊው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሚመረተው የቡና ምርት ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለገበያ እየቀረበ ነው፤ አቅርቦቱም በየዓመቱ እያደገ መጥቷል።  


 
 
ለአርሶ አደሩ በየጊዜው የሚደረገው ድጋፍ፣ ክትትልና ሥልጠና የቡና ጥራትን በተሻለ ሁኔታ መጠበቅ እንዳስቻለም ገልጸዋል።

ዘንድሮ 300 ሺህ ቶን የቡና ምርት መሰብሰቡን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 52 ሺህ ቶን ቡና ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።   
 


 

ጥራት ያለው ቡናን ለገበያ በማቅረብ ሂደት ውስጥ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ድርሻ የላቀ መሆኑንም አመላክተዋል።  
 
የጅማ ዞን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ድማሙ ንጋቱ በበኩላቸው፤ በዞኑ 1 ሺህ 300 መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና 4 ዩኒየኖች እንደሚገኙ ገልጸዋል።   



 
በቡና ምርት ላይ የተሰማሩ ዩኒየኖች በቡና ጥራትና አቅርቦት ላይ በትኩረት እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
 
ዘንድሮ 4 ሺህ 800 ቶን የታጠበና ስፔሻሊቲ ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የዕቅዱን 60 በመቶ ማቅረብ መቻሉን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም