ስዊዲን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ ማጠናከር እንደምትፈልግ አስታወቀች - ኢዜአ አማርኛ
ስዊዲን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ ማጠናከር እንደምትፈልግ አስታወቀች
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፡- ስዊዲን በሁለትዮሽ እና ባለብዙወገን ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ ማጠናከር ትፈልጋለች ሲል የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞትዎስ (ዶ/ር) ከስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያ ማልመር ስቴነርጋርድ ጋር በስቶኮልም ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም፤ በአፍሪካ ቀንድ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።
በዚሁ ወቅትም ሀገራቱ ታሪካዊ እና ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው ያወሱት ሚኒስትሩ፤ ወዳጅነቱን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የሀገራቱን ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት ረገድ የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ነው ያመላከቱት።
የስዊዲን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርበዋል።
የስዊዲን አቻቸው በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያና ስዊድን ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ተናግረዋል።
ስዊዲን በሁለትዮሽ እና ባለብዙወገን ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ ማጠናከር ትፈልጋለች ብለዋል።