በአዲስ አበባ የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በትውልድ ግንባታ ላይ መሠረት እየጣሉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በትውልድ ግንባታ ላይ መሠረት እየጣሉ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2018 (ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ የእናቶችና ሕፃናትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭነት የሚያስቀሩ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በትውልድ ግንባታ ላይ መሠረት እየጣሉ እንደሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።
ቻይልድ ዌልቢንግ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር በሴቶችና ሕፃናት ዙሪያ የሚሰራ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል፡፡
የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብርም "ሕፃናትን መጠበቅ፣ ሴቶችን ማብቃት፣ ጠንካራ የወደፊት ጊዜን መገንባት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ አራዳ ፓርክ ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተወካይ እና በከተማ አስተዳደሩ የስትራቴጂክ ፕሮግራሞች ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እሸትአየሁ ክንፉ (ዶ/ር)፤ በጥቂት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ መገለጫ የነበረው የድህነት ታሪክ የሚቀይር የልማት ድል እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባም የለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልጸጊያን ጨምሮ የትውልድን መፃኢ ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ማዕከላት መገንባታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት በርካታ ማዕከላትን በመገንባት የእናቶችና ሕፃናትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጋላጭነት የሚያስቀር አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
በመንግስትና የልማት አጋሮች የተገነቡ ማዕከላትና የቀዳማዊ ልጅነት መርሃ-ግብርም በትውልድ ግንባታ ላይ መሠረት እየጣሉ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በትውልድ ህይወትና መፃኢ ዕጣ ፈንታን የሚወስኑ የልማት ሥራዎችን ማስፋት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በትውልድ ላይ የሚሰሩ ማዕከላት የሥነ-ልቦና እና ማህበራዊ ፍትሕ ማስፈኛና መስሪያ ስፍራዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የትውልድ ስብራትን የሚያክሙ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የቻይልድ ዌልቢንግ ኢትዮጵያም ዘመናዊ የእናቶችና ሕፃናት ማዕከል በመገንባት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭነትን ለመቀነስ ለሚያደርገው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።
የቻይልድ ዌልቢንግ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በጸሎት እንዳይላሉ፤ "ደህንነቱ የተጠበቀ ሕፃን፥ የነቃች እናት፥ ብሩህ ተስፋ " በሚል መሪ ሃሳብ እናቶችና ሕፃናትን ለመደገፍ እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ድርጅቱ ኢኮኖሚያዊ ተጋላጭ የሆኑ የእናቶችና ሕፃናትን የትምህርትና ጤና አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ የሕፃናት ማቆያ ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለሰው ተኮር ፕሮጀክት ቅድሚያ በመስጠት ለማዕከሉ ግንባታ የሚውል ቦታ በነፃ በመስጠቱ ምስጋና አቅርበዋል።
በጋራ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የአንድ ጊዜ፣ ወርሃዊና ዓመታዊ መዋጮ ጨምሮ የዓይነት፣ የተቋማት አጋርነትና ማህበራዊ ኃላፊነት ትብብሮች ተካሂደዋል።