የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩቱ ምርታማነትን ለማሳደግና አገልግሎትን ለማቀላጠፍ የጀመራቸውን ውጤታማ ተግባራት ማጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩቱ ምርታማነትን ለማሳደግና አገልግሎትን ለማቀላጠፍ የጀመራቸውን ውጤታማ ተግባራት ማጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምርታማነትን ለማሳደግና አገልግሎትን ለማቀላጠፍ የጀመራቸውን ውጤታማ ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል አለበት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት የተቋቋመውን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተገምግሟል።
ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ በግልጽ ራዕይና ቁርጠኝነት ባስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካ አርዓያ መሆኗ ዛሬ ይፋ ተደርጋል።
በዚሁ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) ሆነው መሾማቸው ዛሬ ይፋ ተደርጓል።
ሹመቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፉ ላሳዩት አመራርና ኢትዮጵያ በአህጉሪቷ የሰው ሠራሽ አስተውሎትንና የፈጠራ ሥራዎችን ለማስፋፋት እየተገበረች ላለው የላቀ ሚና የተሰጠ ዕውቅና መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፤ ሹመቱ ኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ሥነ-ምግባራዊ መርሆች በተከተለ መልኩ በማልማት፣ በመመራመር እንዲሁም ተግባራዊ በማድረግ በኩል ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር እንድትሆን ለተሠሩ ሥራዎች ዕውቅና የሰጠ ነው በሚል ገልጾታል።
ይህም አህጉራዊ ትብብር የሚፈጠርበት ብሎም ለዘርፉ ተጨማሪ ኃይል እንደሚሆን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
ዛሬ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር ኢ/ር) ባቀረቡት ሪፖርት፤ የኢንስቲትዩቱን ችግሮች ለመፍታት፣ ብቃትንና ምርታማነትን ለማሳደግ በመረጃ ላይ የተመሰረቱ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ስርዓቶችን ማበልጸግ ላይ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም የሥራ ሂደቶችን በማዘመን የተቋማትን ብቃትና ምርታማነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትጋት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመድፈን ለሀገራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ችግር ፈቺ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ምርምሮችን ማከናወን፣ ማልማት እና ተደራሽ ማድረግን ጨምሮ ምርምሮችን በሳይንሳዊ መጽሔቶች ማሳተም፣ ምርምሮችን ፓተንት ማስገኘት ላይ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።
በግብርና፣ በትምህርት፣ በፋይናንስ፣ በጂኦ ስፓሻል፣ በሮቦቲክስ እና በቋንቋ በዘጠኝ ወራቱ ለመሰብሰብ እና ለማዘጋጀት የሚያስችል መረጃ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።
ችግር ፈቺ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ምርምሮችን ማልማት እና ተደራሽ በማድረግ ረገድ አበረታች ሥራ መሠራቱንም ጠቅሰዋል።
ምርምሮቹን ዓለም አቀፍ ፓተንት የማስገኘት እና የማሳተም ሥራ በታቀደው ልክ መከናወኑንም አብራርተዋል።
የዘርፉን ሥነ-ምኅዳር መገንባት የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ ሀገራዊ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መሠረተ ልማት መገንባቱንም ነው ያስረዱት።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እጸገነት መንግስቱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውጤታማና ለሌሎች አርዓያ መሆን የሚችል አፈፃጸም አስመዝግቧል።
ወጣቶች የሥራ ፈጣሪ እና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ እያከናወነ ያለው ሥራ አበረታች መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በሮቦቲክስ ዘርፍ እየተከናወነ ያለው ሥራና የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ በማሳለጥ ረገድ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
በዘጠኝ ወራቱ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በፋይናንስ፣ በአገልግሎት እና በሌሎች ዘርፎች የታየው አፈፃፀም አበረታች ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የሀገሪቱን ምርታማነት በማሳደግና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑንም አመላክተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 463/2012 ተቋቁሞ በመስከረም 2013 ዓ.ም በይፋ ሥራውን የጀመረ ሲሆን፤ በ2014 ዓ.ም ወደ ኢንስቲትዩትነት በማደግ “አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለሁሉም!” በሚል መሪ ሐሳብ በጤና፣ ግብርና፣ አገልግሎት፣ ፋይናንስ፣ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ፣ ትምህርት እንዲሁም ሌሎች በርካታ ዘርፎች ውስጥ ቴክኖሎጂውን በማልማት ላይ የሚገኝ ተቋም ነው።