ቀጥታ፡

የሕግ ታራሚዎች የልማት ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ሆሳዕና፤ ሚያዝያ 15/2018 (ኢዜአ)፡- የሕግ ታራሚዎችን በሥነ-ምግባር ከማነጽ ባሻገር የልማት ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን አስታወቀ።

20ኛው የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባዔ በሆሳዕና ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።


 

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሕግ ታራሚዎችን በሥነ-ምግባር ከማነጽ ባሻገር የልማት ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ።

የጉባዔው ዓላማ በሀገሪቱ በሚገኙ የማረሚያ ተቋማት የታራሚዎች አያያዝ፣ ማረምና ማነጽ እንዲሁም ፍትሕን በማስፈን ረገድ የጋራ ተግባቦት መፍጠር መሆኑን አስገንዝበዋል።


 

የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብት በማስጠበቅ ረገድ እየተሠራ ባለው ሥራ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርቱካን መንግሥቱ ናቸው፡፡

በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ታራሚዎችን ከማረምና ከማነጽ ሥራ ጎን ለጎን በተለያዩ የሙያ መስኮች እንዲሰለጥኑ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በማረሚያ ቤት ቆይታቸውም ሆነ የእርምት ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ማኅበረሰቡ በሚቀላቀሉበት ወቅት በገቢ ራሳቸውን እንዲደግፉ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡


 

የኦሮሚያ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ረዳት ኮሚሽነር ኢጃራ ጋረደው በበኩላቸው፤ ታራሚዎች እንዲማሩ፣ ተደራጅተው እንዲሠሩ፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች ሥልጠና እንዲያገኙ፣ በጥፋታቸው ተፀፅተው ማኅበረሰቡን እንዲክሱና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም