ቀጥታ፡

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 50 ሚሊየን 514 ሺህ በላይ መራጮች ተመዝግበዋል - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2018 (ኢዜአ)፡- ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 50 ሚሊየን 514 ሺህ በላይ መራጮች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገለጹ።

የሰባተኛው ጠቅላላ የመራጮች ምዝገባ ትናንት ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ተጠናቋል።

ዜጎች በምርጫዬ የሞባይል መተግበሪያ የዲጂታል አማራጭና በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት የመራጮች ምዝገባ አከናውነዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ የምራጮች ምዝገባ መጠናቀቅን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ፤ ቦርዱ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ የዕጩዎችና የመራጮች ምዝገባ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሰረት ከጥር 1 ቀን እስከ የካቲት 1 ቀን ድረስ የዕጩዎች ምዝገባ መከናወኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም ከየካቲት 28 ቀን ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የመራጮች ምዝገባ ለተጨማሪ 14 ቀናት ተራዝሞ ትናንት ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ምሽት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስካሁን በደረሰው መረጃ መሰረት 50 ሚሊየን 514 ሺህ 155 መራጮች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

ከ5 ሚሊየን 503ሺህ በላይ የሚሆኑት መራጮች የተመዘገቡት በዲጂታል አማራጭ ሲሆን ቀሪዎቹ በማንዋል የተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም