የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ረገድ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ረገድ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2018 (ኢዜአ)፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ረገድ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ 16ኛ መደበኛ ስብሰባው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴርን የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የመስኖ ልማት ዘርፉን በማጠናከር ለሀገሪቱ የኢኮኖሚያ ትራንስፎርሜሽን መሠረት የሚጥሉ ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል።
ከመስኖ መሰረተ ልማት አንጻር 100 ሺህ ሄክታር መሬትን ለልማት ዝግጁ ለማድረግ ታቅዶ ከ117 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ዝግጁ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ለረጅም ጊዜ ተጓተው የቆዩ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የነባር ፕሮጀክቶች የጥናትና ዲዛይን ስራ በማሻሻል ግንባታቸውን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ጥረት መደረጉን ጠቅሰዋል።
በዚህም ለረጅም ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች የተጓተቱ ስድስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል።
የአርብቶ አደር አካባቢ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አፈጻጸምን በመተግበር ስትራቴጂክ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በርካታ ስራዎች መከናወኑን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ 61 ፕሮጀክቶች ከዕቅድ በላይ የግንባታ አፈጻጸም ማስመዝገባቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ የሀገሪቱን የዘመናዊ የመስኖ አውታር የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሠራ ተናረዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም የሚኒስቴሩ ሪፎርም ውጤታማነት ምን ደረጃ እንደደረሰ፣ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ምን እንደሚመስል ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፥ ሚኒስቴሩ ባደረገው ሪፎርም አሁን ላይ ውጤታማ ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የተከማቹ የፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናትና ዲዛይን ችግሮችን ለመቅረፍ በርካታ የማሻሻያ ተግባራት በውጤታማነት መቀጠላቸውን ጠቅሰዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈቲሃ አህመድ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ተስፋ ሰጭ ውጤት አስመዝግቧል።
ከ20 ዓመታት በፊት ጥናት እና ዲዛይን የተሰራላቸው፣ ግንባታቸው የተጀመሩ እና ያልተጀመሩ 45 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የጥናትና ዲዛይን ስራ ማሻሻሉን በጥንካሬ አንስተዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የፕሮጀክቶች መጠናቀቅ፣ የአዋጭነት ጥናት፣ የዲዛይን ክለሣ ስራ እንዲሁም ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታር ግንባታ ስራዎች የሚበረታታ መሆኑን በመጥቀስ፥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።