ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ የተጓደሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አመራሮችን ሹመት አፀደቀ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2018 (ኢዜአ)፡- 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ 16ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አመራሮችን ሹመት መርምሮ አጽድቋል። 

የኮሚሽነሮቹን የምልመላ ሂደትና አመራረጥ ሁኔታ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ አቅርበዋል።


 

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ለማሻሻል ባወጣው አዋጅ ቁጥር 1224/2012 አንቀፅ 2/6 መሠረት፤ የተጓደሉ ኮሚሽነሮችን ምልመላ ሲያካሄድ መቆየቱን አስረድተዋል።

ባላቸው የትምህርት ደረጃ እና የሥራ ልምድ አማካይነት ኮሚሽነሮቹ በተደራጀው መልማይ ኮሚቴ መመረጣቸውንም ገልጸዋል። 

በዚህም መሠረት፤ ሚዛኔ አባተ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር፣ ወይዘሮ አሸነፈች አበበ የሴቶችና ሕጻናት ጉዳዮች ዘርፍ ኮሚሽነር፣ አቶ መሀመድ አሕመድ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ጉዳዮች ዘርፍ ኮሚሽነር እና አቶ በዳሳ ለሜሳ የትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ኮሚሽነር አድርጎ ምክር ቤቱ ሹመታቸውን በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።


 

የምክር ቤቱ አባላትም የተመረጡት ኮሚሽነሮች በሥራ ልምዳቸው፣ በሙያና በትምህርት ዝግጅታቸው ኮሚሽኑን ለማገልገልና ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ብቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም