ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና በዲጂታል ጤና ከሀገር በቀል ስኬት ወደ አህጉራዊ መሪነት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና በዲጂታል ጤና ከሀገር በቀል ስኬት ወደ አህጉራዊ መሪነት
(በሙሴ መለሰ)
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዘርፍ እያከናወነች ያለችው ስራ ውጤታማ እንዲሆን ስትራቴጂካዊ የሆኑ ተቋማዊና የፖሊሲ መሰረቶች ተጥለዋል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መቋቋም ለሀገራዊ ችግሮች በቴክኖሎጂ የታገዘ መፍትሄ ለማግኘት ትልቅ አቅም የፈጠረ ሲሆን፣ ብሄራዊ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ ተቀርጾ መጽደቁ ደግሞ የዘርፉን ልማትና አጠቃቀም በተደራጀ መንገድ ለመምራት አስችሏል።
እነዚህ እርምጃዎች ሀገሪቱ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እና 2030 ስትራቴጂ ውስጥ ቴክኖሎጂውን እንደ ቁልፍ የለውጥ አቅጣጫ እንድትጠቀም በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ዘላቂ ለማድረግም በሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቷል።
በአሁኑ ወቅት አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በኮዲንግ፣ በዳታ ሳይንስ እና በክህሎት ለማሰልጠን የተጀመረው ግዙፍ ፕሮግራም የለውጡ አንቀሳቃሽ ኃይል እየሆነ ነው።
ከዚህም ባለፈ፣ በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው የኤአይ ዩኒቨርሲቲ እንዲገነባ መታቀዱና በዚህ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባልነት ውስጥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓት እንዲሳተፍ መወሰኑ፣ ሀገሪቱ ቴክኖሎጂውን ለውሳኔ ጥራትና ለምርምር በከፍተኛ ደረጃ እየተጠቀመችበት መሆኑን ያሳያል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) ሆነው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ጽህፈት ቤቱ እንደገለጸው፣ ሹመቱ የተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፉ ላሳዩት አመራር እና ኢትዮጵያ በአህጉሩ የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የፈጠራ ሥራዎችን ለማስፋፋት እየተገበረች ላለው የላቀ ሚና እውቅና ለመስጠት ነው። በሹመት ደብዳቤው ላይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማስፋፋት ያደረጉት አመራር፣ AI ለአፍሪካ ሉዓላዊነት፣ ለውጤታማነት እና ለአሳታፊ እድገት ቁልፍ መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግል በማስቻል ረገድ ትልቅ እገዛ ማድረጉ ተመልክቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አክሎ እንደገለጸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልታዊ በሆነ መልኩ የቴክኖሎጂ ነጻነትን እና ዐቅምን ለመገንባት የሚያደርጉት ተከታታይ ቅስቀሳ፣ አህጉሩ በኃላፊነት እና በፍትሐዊነት በታጀበ የAI አጠቃቀም ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዲጂታል መሰረተ ልማትን ማስፋፋት፣ የኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት አገልግሎቶችን ሥራ ላይ ማዋል እና በፈጠራ ሥነ-ምህዳር ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ለሀገራዊ ለውጡ ጠንካራ መሰረት የጣሉ ተግባራት መሆናቸውን ጽህፈት ቤቱ በዝርዝር አስፍሯል። በተጨማሪም ራሱን የቻለ የAI ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም የተያዘው ሥራ ምርምርን፣ የክህሎት ልማትን እና አህጉራዊ ትብብርን ይበልጥ እንደሚያጠናክርም ተገልጿል።
ይህ አህጉራዊ እውቅና በተለይ በጤናው ዘርፍ የታዩ ውጤቶችን ያካትታል። ኢትዮጵያ በኤአይ የታገዘ ዲጂታል ኤክስሬይን ለሳንባ ነቀርሳ ምርመራ ካዋሉ የአፍሪካ ሀገራት መካከል በቀዳሚነት ትጠቀሳለች።
በተጨማሪም የ"HEP Assist" መተግበሪያን በሙከራ ደረጃ በማስጀመር፣ በገጠር የሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ውስብስብ ምልክቶችን ሲያዩ ሙያዊ የሕክምና ውሳኔ እንዲሰጡ ድጋፍ እየተደረገ ነው።
እነዚህ የዲጂታል ጤና ስራዎች በ7 ክልሎችና በ15 ወረዳዎች ተግባራዊ መደረግ መጀመራቸው፣ ቴክኖሎጂው በገጠርና በከተማ መካከል ያለውን የአገልግሎት ልዩነት ለማጥበብ ያለውን ፋይዳ ያሳያል።
በአጠቃላይ፣ የኤአይ ቴክኖሎጂ በጤናው ዘርፍ ከሚሰጠው የጡት ካንሰር፣ የአንጎል እብጠትና የቆዳ በሽታዎች ምርመራ ባለፈ፣ በግብርና፣ በፋይናንስና በመንግስታዊ አገልግሎቶች ውስጥም በስፋት እየገባ ይገኛል።
በ2030 በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ሆስፒታሎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል አገልግሎት ለመቀየር የተቀመጠው ግብ፣ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የጀመረችውን የቴክኖሎጂ ነጻነትና የመሪነት ጉዞ ይበልጥ የሚያጠናክር ነው።
በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ሥርዓት በጤና፣ በግብርና እና በመንግስታዊ አገልግሎቶች ውስጥ ለውጥ እያመጣ ይገኛል። በጤናው ዘርፍ እንደ ካንሰር እና ሳንባ ነቀርሳ ያሉ በሽታዎችን ቀድሞ በመለየት የህክምና ጥራትን ሲያሻሽል፣ በግብርናው ደግሞ የሰብል ተባዮችንና የቡና በሽታዎችን በመለየት ምርታማነትን እያሳደገ ነው።
ከዚህ ባለፈም ቴክኖሎጂው በመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ እና በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ሰፊ የመረጃ ትንታኔዎችን በፍጥነት በማከናወን፣ የሥራ ፍጥነትን እና የውሳኔ አሰጣጥ ጥራትን ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገረ ይገኛል።
የዘርፉ ፋይዳ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባለፈ የሀገሪቱን የዲጂታል ሉዓላዊነት እና የሰው ኃይል አቅም በመገንባት ላይ ያተኩራል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን በኮዲንግ እና በዳታ ሳይንስ በማሰልጠን እንዲሁም የፈጠራ ማዕከላትን (Startups) በመገንባት፣ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ በሌሎች ላይ ጥገኛ ከመሆን ወጥታ የራሷን የዲጂታል ኢኮኖሚ መሠረት እየጣለች ትገኛለች።
ይህም በአህጉር ደረጃ ለሚደረጉ የቴክኖሎጂ ሽግግሮች እንደ አርአያ በመሆን፣ ቴክኖሎጂውን ለኢኮኖሚ እድገትና ለማህበራዊ ፍትሃዊነት የመጠቀም ጥቅል ፋይዳው የጎላ እንዲሆን አድርጎታል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሹመት ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ ያላትን የመሪነት ሚና ይበልጥ ያጎላል።
በተጨማሪም ሹመቱ የኢትዮጵያ ተሞክሮ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ማግኘቱንና አፍሪካ በኃላፊነትና በፍትሐዊነት በታጀበ የኤአይ አጠቃቀም ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም እንድትሆን የመሪነት ሚናዋን እንድትወጣም ያደርጋታል።