ከአፍሪካ አቪዬሽን መሪነት እስከ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ትስስር - ኢዜአ አማርኛ
ከአፍሪካ አቪዬሽን መሪነት እስከ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ትስስር
በሙሴ መለሰ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአቪዬሽን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅና በአህጉሪቱ ትልቁ የሆነውን የ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ግዙፍ የኤርፖርት ግንባታ ፕሮጀክት በቢሾፍቱ ከተማ በይፋ መጀመሯን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታውቋል።
ጋዜጠኛ ዳንኤል ኦሊቫሬስ ጋሌጎ በሲኤንኤን የጉዞ ገጽ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ እንደገለጸው፣ ይህ ሜጋ ፕሮጀክት አፍሪካውያን ተጓዦች ከአህጉሩ ውጭ ባሉ እንደ ዱባይ፣ ፓሪስና ለንደን ባሉ ማዕከላት በኩል የሚያደርጉትን አድካሚ ጉዞ በማስቀረት፣ አዲስ አበባን የአህጉሪቱ ቀዳሚ የመገናኛ ማዕከል ለማድረግ ያለመ ነው።
ከአዲስ አበባ ከተማ በስተደቡብ ምስራቅ 48 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ግዙፍ ግንባታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአቪዬሽን መሰረተ ልማት ተብሎ መጠቀሱን ጋዜጠኛው በዚሁ ጽሁፉ አመልክቷል።
ስራው በይፋ የተጀመረው ባለፈው ጥር ወር ሲሆን፣ አውሮፕላን ማረፊያው በ2023 ዓ.ም (2030 እ.ኤ.አ) የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር፣ በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው በሲኤንኤን የጉዞ ገጽ ላይ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፣ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።
ይህም አውሮፕላን ማረፊያውን በዓለም ላይ በርካታ ተጓዦችን ከሚያስተናግደው የአትላንታው ሀርትስፊልድ-ጃክሰን አውሮፕላን ማረፊያ ካለው አቅም በላይ እንደሚያደርገው ዳንኤል ኦሊቫሬስ ጋሌጎ ባሰፈረው ጽሁፍ አብራርቷል።
አውሮፕላን ማረፊያው ከመንገደኞች አገልግሎት ባለፈ፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠናን (AfCFTA) በላቀ ሁኔታ ለመደገፍ ታቅዶ የተገነባ መሆኑን ጋዜጠኛው በሲኤንኤን የጉዞ ገጽ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ በዝርዝር አስቀምጧል።
በዓመት 3 ነጥብ 73 ሚሊዮን ቶን ጭነት የማስተናገድ አቅም ያለው ይህ መሠረተ ልማት፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የአፍሪካን የጭነት በረራ ፍላጎት በሚገባ ምላሽ መስጠት የሚችል መሆኑን ተጠቁሟል።
የአውሮፕላን ማረፊያው የተርሚናል ዲዛይን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ በሆነው ዛሃ ሃዲድ አርክቴክትስ የቀረበ መሆኑን የጠቀሰው ጋዜጠኛው፣ዲዛይኑ የኢትዮጵያን ታላቁ ስምጥ ሸለቆና የተለያየ መልክዓ ምድራዊ ውበትን የሚያንፀባርቅ መሆኑን በጽሁፉ አካቷል።
ተጓዦች በአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ ሲዘዋወሩ የኢትዮጵያን ባህልና ተፈጥሮ እንዲመለከቱ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ሲሆን፣ለዘላቂነት ቅድሚያ በመስጠት የፀሐይ ብርሃን ኃይልንና የዝናብ ውሃ አሰባሰብ ስርዓትን እንዲጠቀም ተደርጎ ተቀርጿል።
በአጠቃላይ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ መጠናቀቅ፣ኢትዮጵያ በአፍሪካ አቪዬሽን ያላትን መሪነት ከማረጋገጡ ባለፈ የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ትስስር ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ጋዜጠኛው በሲኤንኤን የጉዞ ገጽ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ ደምድሟል።
ይህ ፕሮጀክት ከሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር በመተባበር የነጠላ የአፍሪካ አየር ትራንስፖርት ገበያን (SAATM) ወደ ተግባር ለመቀየር የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያግዝም ተመልክቷል።