በአፋር ክልል የንጹህ መጠጥ ውኃ ጥያቄን ለመመለስ የተገነቡ በርካታ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የንጹህ መጠጥ ውኃ ጥያቄን ለመመለስ የተገነቡ በርካታ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገብተዋል
አዋሽ ሰባት፤ ሚያዝያ 15/2018 (ኢዜአ)፡- የንጹህ መጠጥ ውኃ ጥያቄን ለመመለስ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን የአፋር ክልል ርዕሠ መሥተዳድር አወል አርባ ገለጹ።
ከ62 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የአዋሽ ሰባት ከተማ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቅቷል።
ርዕሠ መሥተዳድር አወል በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ በክልሉ የንጹህ መጠጥ ውኃ ጥያቄን ለመመለስ የተገነቡ በርካታ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶቹ መገንባት የሕብረተሰቡን ማኅበራዊና የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የጎላ ድርሻ እንዳላቸው አስገንዝበዋል።
የፕሮጀክቶቹን ፋይዳ ዘላቂ ለማድረግም ሕብረተሰቡ በአግባቡ እንዲጠቀም አሳስበዋል።
የንፁህ መጠጥ ውኃ ፍትሐዊ ተደራሽነትን ለማሳካት መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው ያሉት ደግሞ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ናቸው።
የዛሬው ፕሮጀክት እውን መሆን የከተማ አሥተዳደሩን የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሳደግና ለማዘመን ለሚደረገው ጥረት ተጨማሪ ዐቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የክልሉ ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አህመድ ሻሚ ደግሞ ፕሮጀክቱ ከ650 ሚሊየን ብር በሚልቅ ወጪ መገንባቱን ገልጸው፤ የመጠጥ ውኃ ሽፋንን ለማሳደግ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል።