ቀጥታ፡

ኤክስፖዎች የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት ዐቅምና የእርስበርስ ትስስር እያጠናከሩ ነው

ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚዘጋጁ ኤክስፖዎች የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት ዐቅምና የእርስበርስ ትስስር በማጠናከር ተወዳዳሪነትን ለማላቅ መደላድል እየፈጠሩ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

ድሬ ታምርት፤ ኢትዮጵያ ትበልጽግ በሚል መሪ ሐሳብ በድሬዳዋ የተዘጋጀ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ኤክስፖ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተከፍቷል።



 
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት፤ ኤክስፖዎች የአምራች ኢንዱስትሪዎች የምርት ጥራትና ደረጃን በማሟላት ረገድ የደረሱበትን ከፍታ ለማሳየትና ለሚስተዋሉ ክፍተቶች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እያገዙ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በተጨማሪም የእርስበርስ ትስስርን፣ መመጋገብንና ውድድርን በማጠናከር ሀገራዊ ትልምን ከዳር ለማድረስ ምቹ መደላድል እየፈጠሩ መሆኑን አስረድተዋል።

ከሚያዝያ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ሀገር አቀፍ ኤክስፖ እንደሚዘጋጅም ጠቁመዋል።

በኤክስፖው ላይ ምርታቸውን ያቀረቡ የአምራች ኢንዱስትሪ ተወካዮች በበኩላቸው፤ የግብዓት ልውውጥና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ኤክስፖዎች መዘጋጀታቸው ለአምራች ኢንዱስትሪው ወሳኝ አበርክቶ እንዳላቸው ገልጸዋል።



 
ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተደረገላቸው ድጋፍ ወደ ማምረት የተሸጋገሩ አዳዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም