አምራች ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚ እድገቱ የሚያበረክተውን ሚና ለማጎልበት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
አምራች ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚ እድገቱ የሚያበረክተውን ሚና ለማጎልበት ትኩረት ተሰጥቷል
አርባምንጭ፤ ሚያዝያ 15/2018 (ኢዜአ)፡- አምራች ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚ እድገቱ የሚያበረክተውን ሚና ለማጎልበት ትኩረት መሰጠቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሠ መሥተዳድርና የሥራና ክኅሎት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሠ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ክልል አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር በአርባ ምንጭ ከተማ የተከፈተ ሲሆን፤ የፓናል ውይይትም ተካሂዷል።
አበባየሁ ታደሠ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ አምራች ኢንዱስትሪው ተኪ ምርት ከማምረት አንፃር ያለውን ሚና ለማጉላት በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት አምራች ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚ እድገቱ የሚያበረክተውን ሚና ለማጎልበት ትኩረት መሰጠቱን አረጋግጠዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው፤ አምራች ኢንዱስትሪዎች በሙሉ ዐቅማቸው እንዲያመርቱ የፋይናንስና የኃይል አቅርቦት እንዲሁም የገበያ ችግሮችን ለመፍታት ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ልማትን በማፋጠን ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ በመገንባት ጠንካራ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለመፍጠር በቅንጅት እየተሠራ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሰናይት ሰለሞን ናቸው።
ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከ3 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 30 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰው፤ ለ27 ሺህ 817 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም አስረድተዋል።