በብቁ የሰው ኃይል የተደራጀ የጸጥታ ተቋም እየተገነባ ነው - ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በብቁ የሰው ኃይል የተደራጀ የጸጥታ ተቋም እየተገነባ ነው - ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)
ቦንጋ፤ ሚያዝያ 15/2018 (ኢዜአ)፡- በብቁ የሰው ኃይል የተደራጀ የጸጥታ ተቋም እየተገነባ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሠ መሥተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ተናገሩ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በሞዲዮ የፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም በ1ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን መደበኛ የፖሊስ አባላት አስመርቋል።
ርዕሠ መሥተዳድሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ በክልሉ የፀጥታ መዋቅር ሪፎርም በማድረግ የውስጥ ሰላምና የሕዝብ ደኅንነትን ለማስጠበቅ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል።
በዚህም መሠረት በብቁ የሰው ኃይል የተደራጀ የጸጥታ ተቋም እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነባር የፖሊስ አባላትን ዐቅም ከመገንባት ባሻገር ተልዕኮን መሸከም የሚችል የጸጥታ ኃይል የማፍራት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ተመራቂዎች የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅና ወንጀልን ቀድሞ በመከላከል የተጣለባቸውን ሕዝባዊ አደራ በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል።
የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ተግዳሮት የነበረውን የሰው ኃይል እጥረት ለመመፍታት እየተሠራ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ካሳ ናቸው።
ዛሬ የተመረቁ የፖሊስ አባላትም፤ በሕገ መንግሥት፣ በወንጀል እና በትራፊክ አደጋ መከላከል እንዲሁም በሌሎችም መሰል ጉዳዮች ሥልጠና ማግኘታቸውን አብራርተዋል።
የክልሉ ሠላምና ፀጥታ አሥተዳደር ቢሮ ኃላፊ አንድነት አሸናፊ በበኩላቸው፤ በክልሉ ያለውን ሰላም በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።