የሂሳብ ትምህርትን አቀራረብ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሂሳብ ትምህርትን አቀራረብ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ ይገባል
ደሴ፤ ሚያዝያ 15/2018 (ኢዜአ)፡- የሂሳብ ትምህርት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ ተወዳጅና ተመራጭ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሂሳብ ባለሙያዎች ማኅበር ገለጸ።
ማኅበሩ 3ኛውን ዓመታዊ የምርምር ኮንፈረንስ በወሎ ዩኒቨርሲቲ እያካሄደ ነው።
በዚሁ ወቅትም የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል አሰፋ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የሂሳብ ትምህርት ለሳይንስ፣ ለቴክኖሎጂና ለሌሎች ዘርፎች መሰረት ስለሆነ የትምህርት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ ይገባል።
የሂሳብ ትምህርትን ተግባር ተኮር የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ በመጠቀም ማስተማር እንደሚገባም አመላክተዋል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሀገራዊ ምርምርና ልማት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሀብታሙ አበራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሂሳብ ትምህርት ላይ የተመሰረተ የዳታ ሳይንስና የቴክኖሎጂ እድገትን ለማስመዝገብ ከማኅበሩ ጋር እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ባለሙያዎችን በማብቃት የሂሳብ ትምህርት ለዲጂታል ኢኮኖሚው ግብዓት እንዲሆን እየተሠራ ነው ብለዋል።
በሂሳብ ልዩ ተሰጥዖና ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች በክረምት ጭምር ተጨማሪ ትምህርት በመስጠት እንዲበቁና እንዲመራመሩ እየተደረገ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ብርሃን አስማሜ (ዶ/ር) ናቸው።
በኮንፈረንሱ ላይ 16 የምርምር ውጤቶች እንደሚቀርቡም ተመላክቷል።