24ኛው ሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ የቁንጅና ውድድር ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
24ኛው ሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ የቁንጅና ውድድር ተካሄደ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ የተዘጋጀው የቁንጅና ውድድር ለ24ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ-ጥበብ ስነ-ጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት ቁንጅና እና ውበት በሰብዓዊም ሆነ በመልክዓምድራዊ ገጽታ ኢትዮጵያን የሚገልጥ ሃብት ነው፡፡
መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያ ወግ፣ ባሕልና ሀገራዊ እሴት በልጆቿ እንዲገለጥ እና ለዓለም እንዲታይ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ አዘጋጅነት ላለፉት 24 ዓመታት ሲካሄድ የቆየው የቁንጅና ውድድር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ መልክ ለዓለም ማስተዋወቁንም ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ የነበረችው ሞዴል ሀሴት ደረጀን አስተዋፅኦ በማስታወስም ተወዳዳሪዎች ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በ24ኛው የሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ የቁንጅና ውድድር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰቡ 50 ቆነጃጅት የተሳተፉ ሲሆን ራሳቸውን በመግለጽ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ 25 ተወዳዳሪዎች ተለይተዋል።
በውድድሩ ወይዘሪት ሩት ይርጋለም ኢትዮጵያን በዓለም የምትወክለዋ ቆንጆ ሆና በመመረጥ የ2026 ሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ አሸናፊ የክብር ዘውድን መድፋት ችላለች።
አሸናፊዋ በቀጣይ ኢትዮጵያን በመወከል በሚስ ወርልድ የዓለም ቁንጅና ውድድር ላይ የምትሳተፍ መሆኑንም ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።