ቀጥታ፡

ደብረ ብርሀን ከተማ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ማዕከል እየሆነች ነው

ደብረ ብርሃን፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦ደብረ ብርሃን ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ማዕከል እየሆነች መምጣቷን የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት አስታወቁ። 

በአትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ በ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወጪ በደብረ ብርሃን ከተማ የተገነባው ባለ 4 ኮከብ ዘመናዊ ሆቴል ዛሬ ተመርቋል።  


 

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አቶ በድሉ ውብሸት በሆቴሉ ምረቃ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት፤ የደብረ ብርሃን ከተማ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ማዕከል እየሆነች መጥታለች።


 

ዛሬ የተመረቀው ባለ 4 ኮከብ ዘመናዊ ሆቴልም ከተማዋ ታላላቅ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንሶችን ለማስተናገድ ተመራጭ እንድትሆን የሚያስችላት መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በከተማዋም ሆነ በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር ያግዛል ብለዋል፡፡

ሆቴሉ ለከተማዋ ወጣቶች ተጨማሪ የሥራ ዕድል የሚፈጥርና የከተማዋን ገጽታ የሚገነባ መሆኑን ጠቁመው የከተማ አስተዳደሩ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ በበኩላቸው፤ ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ በአትሌትነት ጊዜው "የይቻላል" መንፈስን ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች ያስተማረ ጀግና ነው ብለዋል።


 

በደብረብርሃን ከተማ ያስገነባው ሆቴል ዞኑን የቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪና የኮንፈረንስ ማዕከል በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

የሃይሌ እና ዓለም፤ ዓለም አቀፍ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ ባለቤት አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ እንደገለጸው፤ በሆቴልና ሪዞርት ዘርፍ ኢትዮጵያ ፈጣን እድገት እንድታስመዘግብ የበኩሉን እየተወጣ ነው።

ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ በ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ተገንብቶ የተመረቀው ባለ 4 ኮከብ ሆቴልም የድርጅቱን የሆቴሎችና ሪዞርቶች ቁጥር ወደ 11 በማሳደግ በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላል ብሏል።


 

ሆቴሉ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ መገንባቱንና ዘመናዊ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የተሟላ ጂምናዚየም እና ልዩ ልዩ  አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ተደርጎ የተገነባ መሆኑን አብራርቷል።

ሆቴሉ በአሁኑ ወቅት ለ200 ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ የሥራ እድል ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ300 በላይ እንደሚሆንም አመልክቷል።

በቀጣይም በጎንደር፣ በሐረር እና በድሬዳዋ ከተሞች አዳዲስ መዳረሻዎች በማስገንባት በዘርፉ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም