ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ የላቀ ውጤታማነት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን እንደ ወሳኝ ግብዓት እየተጠቀመች ትገኛለች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ እያከናወነች ያለችውን ውጤታማ ሥራ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን እንደ ወሳኝ ግብዓት እየተጠቀመች መሆኑን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው "የአካባቢ ብክለት ዲጂታል ሪፖርት ማድረጊያ ሥርዓት" በይፋ ስራ አስጀምሯል።


 

ይህ አዲስ የዲጂታል ቴክኖሎጂ የአካባቢ ጥበቃና የብክለት ቁጥጥር ሥራን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ የዳታ ትንተና በማከናወን ለማዘመን ያለመ ነው።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ተቋሙ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ "ኤ.አይ ለሁሉም" በሚል መርህ ሀገራዊ የልማት ግቦችን የሚደግፉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እያመረተ ይገኛል።

ይህ ዛሬ ይፋ የሆነው መተግበሪያም ህብረተሰቡ የብክለት ጥቆማዎችን በቀላሉ እንዲያደርስና በፈጣን የዳታ ትንተና አማካኝነት ተገቢው ምላሽ እንዲሰጥ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሃጽዮን ፤ መንግሥት የአሁኑንና የቀጣዩን ትውልድ ተጠቃሚነት ታሳቢ ባደረገ የኢኮኖሚ ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ዛሬ ይፋ የሆነው ዲጂታል መተግበሪያ መንግሥት በዘርፉ የሚወስዳቸውን የፖሊሲ ማሻሻያዎችና ፈጣን ምላሾች በዳታ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ለማድረግ እንደ ግብዓት የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሌሊሴ ነሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መተግበሪያው በተለይ በከተሞች የተገነቡ የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ እና የጽዳት ሥራዎችን በዘላቂነት ለመጠበቅ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።


 

ቴክኖሎጂው ተቋማቸው በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲወስንና የብክለት ምንጮችን በቅርበት መቆጣጠር የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

በመሆኑም ፅዱ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ህብረተሰቡ በንቃት በመሳተፍ ጥቆማዎችን በመተግበሪያው በኩል እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ የዲጂታል ሪፖርት ማድረጊያ መተግበርያ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራና በከተሞች ውበት ላይ የጀመረቻቸውን ስኬታማ ሥራዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስደገፍ የተሻለ የአየር ንብረት ለመፍጠር ለሚደረገው ጉዞ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም