ቀጥታ፡

በክልሉ እየተገነቡ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው

ጂንካ፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተገነቡ ከሚገኙ 11 አነስተኛ ፕሮጀክቶች 7ቱን በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በክልሉ ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ቦክሬ ቀበሌ በሚገኘው የቱርሞ ወንዝ ላይ ለሚገነባው አነስተኛ የመስኖ አውታር ግንባታ ፕሮጀክት ከተቋራጩ ጋር የውል ስምምነት ተፈራርሟል።


 

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የቢሮው ኃላፊ አቶ ኤካል ነትር፣ በክልሉ አርሶና አርብቶ አደር አካባቢዎች 11 አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በግንባታ ላይ ካሉ 11 ፕሮጀክቶች 7ቱን በዚህ ዓመት እስከ ነሐሴ ወር ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ከሚጠናቀቁት ፕሮጀክቶች መካከል ብላቴ ኤታ፣ ማርቃላሾ፣ ማዜ፣ ሎማቴ፣ አርጎ፣ ካራዱስ እና ሳላ የተባሉት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ጭሮ፣ ኩላኖ፣ ሱጋሌ እና ዛሬ የውል ስምምነት የተፈፀመበት የቱርሞ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክት ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጠናቀቁም አስረድተዋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ እና የመስኖ ልማት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢሳያስ ቢፍቱ፥ መንግስት በአርሶ እና አርብቶ አደሩ አካባቢ የመስኖ አውታሮችን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

በተለይ በቆላማ አካባቢ የሚገኙ ማህበረሰቦችን በመስኖ ልማቱ በማሳተፍ የተጀመረው ልማት ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በቀጣይም አርሶና አርብቶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በመስኖ ልማቱ ምርታማነታቸውን በእጥፍ የሚያሳድጉበት ሁኔታ ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ዛሬ የተጀመረው የቱርሞ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክትም ከ71 ሄክታር በላይ ማልማት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው ከ103 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደተመደበለትም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱን በ6 ወራት ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

የቱርሞ ፕሮጀክት ከአለም ባንክ በተገኘ ብድር በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ድጋፍ ከሚተገበሩ የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑንም አንስተዋል።


 

ግንባታውን የተረከበው በረከት ተሾመ የውሃ ስራዎች ተቋራጭ ባለቤት አቶ በረከት ተሾመ፤ ግንባታውን በፍጥነት፣ በጥራትና በተያዘለት ቀነ ገደብ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቱ የቱርሞ ወንዝን በመገደብ ከከፍታ ቦታ ወደ ዝቅተኛ ቦታ በማፋሰስ ለእርሻ ልማት የማዋል ፅንሰ ሀሳብን የያዘና ይህም ተግባር ነዳጅም ሆነ የኤሌክትሪክ ኃይልን የማይጠቀም በመሆኑ አዋጭ የመስኖ አውታር እንደሆነም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም