በክልሉ ለተመዘገበው ልማትና መልካም አስተዳደር የምክር ቤቶች ሚና ከፍተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለተመዘገበው ልማትና መልካም አስተዳደር የምክር ቤቶች ሚና ከፍተኛ ነው
ሚዛን አማን፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለተመዘገበው ልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መጠናከር ምክር ቤቶች የላቀ ሚና እንደነበራቸው ተገለጸ ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤትና የዞን ምክር ቤቶች የጋራ ምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ለ7ኛ ጊዜ የሚደረገው የጋራ የምክክር መድረክ የልምድ ልውውጥና ውጤታማ ተሞክሮዎች የሚቀመሩበት ነው ።
ምክር ቤቱ ከሕዝብ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የምክር ቤቶችን አደረጃጀት በማጠናከርና የክልሉ ሕገ መንግስት ያስቀመጣቸውን ኃላፊነቶች በተገቢው መንገድ በመፈፀም ላይ ነው ብለዋል።
ከዚህ ውስጥም ባለፉት ዓመታት የአስፈጻሚ አካላት ተግባራት ላይ ክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር በማድረግ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና ልማቶች በተገቢው መንገድ እንዲከናወኑ የድርሻውን መወጣቱን አስረድተዋል ።
በዚህም የሕዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ሥራዎች በስፋት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የመንግስት የልማት ኢኒሼቲቮች የዜጎችን ኑሮን ለማሻሻል የሚያስችሉ በመሆናቸው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው መተግበር እንዲችሉ ምክር ቤቶቹ ጥረት እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ጌድዮን ኮስታብ በበኩለቸው፤ በሕዝቦች መካከል አንድነትና የእርስ በእርስ ትስስርን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የዞኑን የልማት ሥራዎች መስክ ላይ ወርዶ በመከታተልና አቅጣጫ በማሳየት መልካም ተሞክሮዎች እንዲያድጉ ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን ያጠናክራል ብለዋል።
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የምክር ቤቶቹ የጋራ የምክክር መድረክ ላይ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤን ጨምሮ የስድስቱም ዞኖች አፈ ጉባኤዎችና ቋሚ ኮሚቴዎች ተገኝተዋል።