ቀጥታ፡

ባህልን በአግባቡ በማልማት እና በማስተዋወቅ ለሀገር እድገት ማዋል ይገባል

ጅማ ፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦ነባር ባህላዊ እሴቶችን በቴክኖሎጂ ታግዞ በማልማት እና በማስተዋወቅ ለሀገር እድገት መጠቀም ወሳኝ መሆኑ ተመላከተ።   

በጅማ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ በሚገኘው 6ኛው ዓለም አቀፍ የኦሮሞ ጥናት ኮንፈረንስ ላይ ባህልን ዲጂታላይዝ በማድረግ ለሀገር እድገት ስለማዋል ያለመ ውይይት እየተደረገ ነው።   


 

በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ኡቱካና ኦዳ (ዶ/ር)፤ ባህልን በመጠበቅና በመንከባከብ ለሀገር እድገት ማዋል እንደሚገባ አሳስበዋል።   

ባህል ቋንቋ ወይምነባር እሴቶች ብቻ ሳይሆን፣ ባህልን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት ዓለም አቀፋዊ የማድረግ ስራን ይጨምራል ብለዋል።   

"በተለይም ዘመን ተሻጋሪ ባህላዊ እሴቶችን ዘመኑን በዋጀ መልኩ በመጠበቅና ዲጂታላይዝ በማድረግ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ልንጠቀምበት ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል።   

 ለዚህ ስኬት ደግሞ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራን የላቀ ድርሻ እንዳላቸው ጠቁመዋል።  


 

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ባህል ለሀገር ሰላምና አንድነት ያለውን ሚና ገልጸው፣ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 10 ዓመታት በዚህ ዘርፍ በስፋት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።   

ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች 12 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት በኦሮሞ ባህል ጥናት ላይ የጀመረው ስራ ተጨባጭ ለውጦችን እያመጣ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ "የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮች የዜጎችን ሕይወት በሚቀይር መልኩ ወደ ህዝብ መውረድ አለባቸው" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።   

በዚህ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ ከተለያዩ የምርምር ተቋማት የተጋበዙ ተመራማሪዎች የጥናት ጽሑፍ እያቀረቡ ሲሆን፤ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም