ቀጥታ፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለአቅመ ደካሞች ያስገነባቸውን መኖሪያ ቤቶች አስረከበ

ወረር አዳብቶሌ፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአፋር ክልል በተለያዩ ከተሞች ለአቅመ ደካማ ወገኖች ያስገነባቸውን መኖሪያ ቤቶች አስረከበ።

ዛሬ የተረከቡት መኖሪያ ቤቶች በክልሉ ወረር አዳብቶሌ፣ ዱብቲ እና አዋሽ ከተሞች የተገነቡ 16 መኖሪያ ቤቶች ናቸው።

በቤቶቹ ርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ፤ማኀበራዊ ሀላፊነትን በትብብር መወጣት መቻል የሚያስመሰግንና መጠናከር ያለበት መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከሁሉ በላይ አቅመ ደካሞችን በማገዝ አብሮነትን ማሳየት የሚያስደስት ተግባር መሆኑን ገልጸው፣ ይህን በጎ ተግባር ላከናወነው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ የበጎነት አሻራን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እያሳረፈ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ወረር አዳብቶሌ፣ ዱብቲ እና አዋሽ ከተሞችም ባለፈው የክረምት ወራት ግንባታቸው የተጀመሩ 16 የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶችን በዛሬው እለት ማስረከቡን ተናግረዋል።

እርስ በርስ የመተጋገዝ ባህልን ለማስቀጠል በተለያየ ችግር ውስጥ ላሉ አቅመ ደካሞች ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት መገንባቱን ገልጸው፣ ለቤቶቹ ግንባታ 62 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ብለዋል።


 

ሚኒስቴሩ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ የጀመረውን የበጎ አገልግሎት ሥራ ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ ክልል ሞጆና ዱከም ከተሞች ማስቀጠሉንም አስታውሰዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ውጤት እየተገኘበት መሆኑንም አመልክተዋል።

የወረር አዳብቶሌ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አብዱ ጉራ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ ያደረገው ድጋፍ በመተጋገዝ ማህበራዊ ኀላፊነትን ከመወጣት ባለፈ አቅመ ደካሞችን መታደግ እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል። 


 

ዛሬ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ለተደረገው ድጋፍ በከተማ አስተዳደሩ ሥም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም