ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥና የራስን አቅም የመገንባት ታሪካዊ ጉዞ ነው 

ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገርን የኢኮኖሚ ነፃነት በማረጋገጥ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ታሪካዊ ጉዞ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ይህን የተናገሩት "ድሬ ታምርት ኢትዮጵያ ትበልፅግ" በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው የአምራች ኢንዱስትሪዎች ኤክስፖ የፓናል ውይይት ላይ ነው።


 

አቶ መላኩ በወቅቱም፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ በተደረገው ድጋፍና ክትትል እመርታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በንቅናቄው የተዘጉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲመለሱ በማድረግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በጥራትና በስፋት እየተተኩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በማምረት፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ እና የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድም መሠረታዊ ውጤቶች መገኘታቸውን በመጥቀስ።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገርን የኢኮኖሚ ነፃነት በማረጋገጥ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ታሪካዊ ጉዞ መሆኑን በአፅንኦት ገልጸዋል።

በሌሎች ሀገራት አልባሳት፣ መድኃኒት፣ መገልገያዎችና ሌሎች ምርቶች ላይ ጥገኛ የሆነ አገር ሉዓላዊነቱን ማረጋገጥ እንደማይችል በማመላከት።

በንቅናቄው በተሰሩ ስራዎች በዘንድሮ በጀት ዓመት ብቻ 13 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገቡ የውጭ ሀገራት ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በዘርፉ ለመሰማራት መዘጋጀታቸውን አስታውሰዋል።

ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግና በኢኮኖሚው ውስጥ የመሪነት ድርሻውን እንዲያረጋግጥ የህግና የፖሊሲ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ይገኛሉም ብለዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በተደረጉ ድጋፎች  ተዘግተው የነበሩ 15 ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ማምረት በማሸጋገር ከ9 ሺህ 200 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ተኪ እና ወጪ ምርቶችን በስፋትና በጥራት እያመረቱ መሆኑን ጠቅሰው ከንቅናቄው በኋላ የኢንዱስትሪዎቹ የማምረት አቅም ከ42 በመቶ ወደ ወደ 64 በመቶ ከፍ ማለቱን አንስተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ፤ ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተሰሩ ስራዎች ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻላቸውን ገልፀዋል።


 

በተደረጉ ሁሉን አቀፍ ድጋፎችና ክትትሎች የተዘጉ እና በግንባታ ላይ ያሉ ፋብሪካዎች ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን በማስታወስ።

ባለፉት ዓመታት 253 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ከ2 ሺህ 620 በላይ ባለሃብቶች ፍቃድ ወስደው ወደ ዘርፉ  መግባታቸውን ጠቅሰው ወደ ማምረት የተሸጋገሩትም ከ10ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል ብለዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ባለቤቶች፣ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም