ቀጥታ፡

የተሻለ ውጤት በማምጣት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመግባት ዝግጅት እያደረግን ነው- የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች

ሰቆጣ፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት በማምጣት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመግባት ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰቆጣ ከተማ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ገለፁ።

በሰቆጣ ከተማ የዋግ ስዩም አድማሱ ወሰን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ለምለም መኮንን ለኢዜአ እንደገለጸችው፤ በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች።


 

ትምህርት ቤታቸው ከመደበኛው የትምህርት ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ በትርፍ ጊዜያቸው የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ ቤተመጻህፍትን ክፍት በማድረግና መጻህፍትን በማሟላት  እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግራለች።

በተጨማሪም ከክፍል ጓደኞቿ ጋር እርስ በእርስ በመረዳዳትና ያለፉትን ዓመታት የፈተና ጥያቄዎች በቡድን በመስራት የተሻለ ውጤት በማምጣት ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያስችላቸውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አስረድታለች።

ተማሪ ሳህለ ጊዮርጊስ ደባሹ በበኩሉ ለፈተናው ከተማሪዎች ጋር በመሆን እየተጋገዙ በቂ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጿል።


 

መምህራንም በመደበኛው የትምህርት ጊዜ ለፈተናው በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ በሚያስችል መልኩ እውቀት እያስጨበጧቸው መሆኑን ተናግሯል።

ትምህርት ቤቱ የዲጂታል መማሪያ ክፍል በማዘጋጀትም በኦን ላይን የሚሰጠውን ፈተና ቀድመው እንዲለማመዱ እያደረገ ነው ብሏል።

በትምህርት ቤቱ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ሰፊው ሃብቱ እንደገለጹት፤ ተፈታኝ ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ለፈተናው በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ እገዛ እየተደረገ ነው።


 

ያለፉ የፈተና ጥያቄዎችን በማሰራት፣ በስነ ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ በማድረግና በፈተና ወቅት መረጋጋት አስፈላጊ መሆኑን በማስገንዘብ ዝግጅታቸውን ወደ ውጤት እንዲቀይሩት እያስረዳን እንገኛለን ብለዋል።

የዋግ ብሔረሰብ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ፍትሃለሽ ምረቴ ፤ በአስተዳደሩ 3 ሺህ 506 ተማሪዎች የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንደሚወስዱ ተናግረዋል።


 

ተፈታኝ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የመርጃ መፅሀፍትን በማሟላት፣ ቤተ መጻህፍቱን እንዲጠቀሙ በማድረግና የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም