ቀጥታ፡

ለህብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅተናል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦ ለህብረተሰቡ የተለያዩ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መንገድ ለመስጠት ተዘጋጅተናል ሲሉ የመሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ሰራተኞች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአይነቱ ልዩና የመጀመሪያ የሆነውን መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት አስጀምረዋል።

በአገልግሎቱ የስምንት ተቋማትን አገልግሎቶች በአንድ ላይ በማቀናጀት በይፋ ስራ የጀመረ ሲሆን፤ ይህም ለህዝብ የሚሰጡ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ይበልጥ ተደራሽ እና ቀልጣፋ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።


 

በዚህ ተንቀሳቃሽ የአውቶቡስ አገልግሎት የተጀመሩ አገልግሎቶችም፣ የገቢ (አዲስ ቲን ማውጣት)፣ የንግድ (ንግድ ፈቃድ ማውጣት፣ ማደስ)፣ የጤና (ለመንጃ ፈቃድ አካላዊ የጤና ምርመራ)፣ የሲቪል ምዝገባ (የመታወቂያ ዕድሳት እና ልደት)፣ የአሸከረካሪ ተሽከርካሪ (የመንጃ ፈቃድ እና የቦሎ ዕድሳት)፣ የኢትዮ ፖስታ (የመንገድ ፈንድ ክፍያ)፣ የብሔራዊ መታወቂያ (አዲስ ምዝገባና የመረጃ እርማት) እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት (ቅድመ ክፍያ) ናቸው።

በመሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት እንዲሰጡ የተመደቡ የልዩ ልዩ ተቋማት ሰራተኞች፣ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በዘመናዊና ቀልጣፋ መንገድ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

በሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የአዲስ መሶብ አገልግሎት አስተባባሪ ዳኜ መኮንን ኤጀንሲው በተንቀሳቃሽ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ላይ ለህብረተሰቡ ከሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ጋር የተገናኙ አስር ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት ወደ ስራ ገብተናል ብለዋል።


 

ለአገልግሎት ፈላጊ ደንበኞች ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች መካከል የዲጂታል መታወቂያ እድሳት፣ የልደት ካርድ ማውጣት፣ የጉዲፈቻና ያላገባ ሰርተፊኬት መስጠት ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የመሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ውስጥ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የደንበኞች አገልግሎት ባለሙያ አስናቀ ወርቁ በበኩላቸው፣ ባለስልጣኑ በማዕከሉ የመንጃ ፈቃድ እድሳትን፣ የዓመታዊ የብቃት ማረጋገጫ ቦሎና የተበላሸ ቦሎ ግልባጭ እንዲሁም የጠፋ ቦሎ ምትክ የመስጠት አገልግሎቶችን ለደንበኞች እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።


 

በመሶብ ተንቀሳቃሽ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የጤና ምርመራ ዘርፍ የሚያገለግሉት አቶ ጉቱ ከበደ በበኩላቸው፤ በተለይም ለመንጃ ፈቃድ ዕድሳት የሚመጡ ደንበኞችን ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች አስፈላጊ የጤና ምርመራዎችን በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል።


 

በገቢዎች ቢሮ የደንበኞች አገልግሎት ባለሙያ ጫልቱ ታደሰ፣ ቢሮው ከሚሰጣቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰውን የንግድ መለያ ቁጥር (ቲን ነምበር) የመስጠት ተግባር በተንቀሳቃሽ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አማካኝነት ለነዋሪዎች እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ፖስታ ባለሙያ ሙላቷ አበዙ ድርጅታቸው በመሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ውስጥ የመንገድ ፈንድ አገልግሎት እና የፋይዳ መታወቂያ ህትመት የሚፈልጉ ደንበኞችን ለማስተናገድ መዘጋጀቷን ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም