የማረሚያ ተቋማት የስብዕና እና የክህሎት ግንባታ ማዕከል ሆነው እንዲያገለግሉ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማረሚያ ተቋማት የስብዕና እና የክህሎት ግንባታ ማዕከል ሆነው እንዲያገለግሉ እየተሰራ ነው
ሆሳዕና፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማረሚያ ተቋማት የስብዕና እና የክህሎት ግንባታ ማዕከል ሆነው እንዲያገለግሉ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።
የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ “የማረሚያ ተቋማት ለሀገር ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በሆሳዕና ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በክልሉ የማረሚያ ተቋማት የስብዕና እና የክህሎት ግንባታ ማዕከል ሆነው እንዲያገለግሉ እየተሰራ ነው፡፡
በክልሉ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎችን በስነ ምግባርና በክህሎት ለማነጽ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ዛሬ የተጀመረው የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ጉባኤ በክልሉ የተጀመረውን የሪፎርምና የተቋም ግንባታ ሥራን ለማጠናከር ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ብለዋል፡፡
ለሦስት ቀናት እየተካሄደ ባለው ጉባኤ በማረሚያ ቤቶች እየተከናወኑ ባሉ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ላይ በመምከር የቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም ከታራሚዎች የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ መሰረታዊ ፍላጎት አቅርቦት፣ ከማረሚያ ቤት የሪፎርም ሥራዎች እንዲሁም ከማረም ማነጽ ተሀድሶ ልማት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ጉባኤው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመክር ታውቋል።
በመድረኩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ የፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን እንዲሁም ከክልል ማረሚያ ቤቶችና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጡ የሥራ ኃላፊዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።