ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ ሆነው ተሾሙ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) ሆነው ተሹመዋል።

ሹመቱ የተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዘርፉ ላሳዩት አመራር እና ኢትዮጵያ በአህጉሩ የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የፈጠራ ሥራዎችን ለማስፋፋት እየተገበረች የምትገኘውን የላቀ ሚና እውቅና ለመስጠት ነው።

በተላከው የሹመት ደብዳቤ ላይ "የተከበሩ የእርስዎ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት ያደረጉት አመራር፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ለአፍሪካ ሉዓላዊነት፣ ለውጤታማነት እና ለአሳታፊ እድገት ቁልፍ መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግል በማስቻል ረገድ ትልቅ እገዛ አድርጓል" የሚል ሀሳብ መስፈሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል። 

"ስልታዊ በሆነ መልኩ የቴክኖሎጂ ነጻነትን እና ዐቅምን ለመገንባት የሚያደርጉት ተከታታይ ቅስቀሳ፣ አህጉሩ በኃላፊነት እና በፍትሐዊነት በታጀበ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል" የሚል መልዕክትም በተላከው የሹመት ደብዳቤ ላይ ሰፍሯል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር፣ ኢትዮጵያ በዲጂታላይዜሽን እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፎች ያስመዘገበችው እድገት ከፍተኛ አፈጻጸም ማሳየቱን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

የዲጂታል መሰረተ ልማትን ማስፋፋት፣ የኢ-መንግሥት አገልግሎቶችን ሥራ ላይ ማዋል፣ በፈጠራ ሥነ-ምህዳር ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩትን ማቋቋም እንዲሁም ሀገራዊ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስትራቴጂ መንደፍ ለለውጡ ጠንካራ መሰረት የጣሉ ተግባራት መሆናቸውንም አክሎ ገልጿል።

በተጨማሪም ራሱን የቻለ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም የታቀደው ዕቅድ፤ ምርምርን፣ የክህሎት ልማትን እና አህጉራዊ ትብብርን ይበልጥ እንደሚያጠናክር የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም