ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዣን ካሴያ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ጠዋት የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ከዶክተር ዣን ካሴያ ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

በውይይታቸውም በተለያዩ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል፡፡

በተለይም በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) በመሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተሰጣቸውን አዲስ ኃላፊነት በሚመለከት በስፋት መነጋገራቸውን ጠቁመዋል።

የፈጠራ ሥራዎች ለአፍሪካ ዕድገት ምንጊዜም ወሳኝ መሰረት ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጤናው ዘርፍ የሚገጥመንን ተለዋዋጭ ተግዳሮቶች ለመወጣት የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ዐቅም መጠቀም የጤና ሥርዓታችንን ለማጠናከር፣ ተደራሽነትን ለማስፋፋት እና ለሕዝባችን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ልምድ ለአህጉሩ ለማካፈል እንዲሁም በፍጥነት ከሚለዋወጠው የቴክኖሎጂው ዓለም ጋር ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመራመድ የሚያስችሉ ጠንካራ አጋርነቶችን ለመመሥረት ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም ማረጋገጧንም ገልጸዋል።

ይህንን ርዕይ ወደ ተጨባጭና አካታች ውጤት ለመለወጥ ከአፍሪካ ሲዲሲ (Africa CDC) እና በመላው አህጉሪቱ ከሚገኙ አጋሮች ጋር በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ ነኝ  ሲሉም አስፍረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም