ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን በማዕድን ዘርፍ ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ተችሏል

ገንዳውኃ፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦በምዕራብ ጎንደር ዞን በለውጡ መንግስት ልዩ ትኩረት በተሰጠው የማዕድን ዘርፍ ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ መቻሉ ተገለጸ።

​የዞኑ ማዕድን ሀብት መምሪያ ኃላፊ ተወካይና የማዕድን ሥራዎች ፈቃድ አስተዳደር ባለሙያ አቶ ወረቀት ቆየ ለኢዜአ  እንደገለጹት፤ ዞኑ እምቅ የማዕድንና ግብርና ኢንቨስትመንት ሃብት ያለው ነው። 


 

በዚህም በዞኑ ባለፉት 9 ወራት ያለውን ማእድን ለማልማት በተደረገ ጥረት በ32 ማህበራት ለተደራጁ ከ470 በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

የስራ ዕድሉን መፍጠር የተቻለውም በኦፓል፣ በጥቁር ድንጋይና በነጭ አሸዋ ማውጣት መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ በተደጋጋሚ በተጠናው ጥናት መሰረት የወርቅ፣ የብረት፣ የኦፓል፣ የጄሶ፣ የሲልካ፣ የመዳብና የኒኬል ማዕድናት በስፋት እንደሚገኙ መረጋገጡን አስረድተዋል።


 

በቀጣይ ከክልሉ ጋር በመነጋገርና ባለሃብቶችን ወደ አካባቢው በመሳብ የማዕድን ሃብቱን በማልማት ተጨማሪ የስራ እድል ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል። 

ከማዕድን ልማቱም ገቢ በመሰብሰብ ለልማት ማዋል መቻሉን ጠቁመው የመጣውን ሰላም በመጠቀም በቀጣይ የስራ እድል ፈጠራውን ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።

​በገንዳውሃ አካባቢ በአሽዋና በድንጋይ ማዕድን ልማት ስራ ላይ በመደራጀት ወደ ስራ ከገቡ ወጣቶች መካከል ወጣት ዮሴፍ ዳኘ እንደገለጸው፤ በከተማዋ ለሚካሄደው የኮሪደር ልማት ግብዓት በማቅረብ ውጤታማ ሆነዋል። 

በባህላዊ መንገድ ማዕድን በማውጣት ዘርፍ ላይ የተሰማሩት አቶ ምህረት ደጀኔ በበኩላቸው፤ በመንግሥት በኩል እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል። 

በተለይ ህገ-ወጥ የማዕድን ዝውውርን በመከላከልና የተደራጁ ዜጎች ሰርተው እንዲለወጡ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም