ቀጥታ፡

በምሥራቅ ወለጋ ዞን በመጪው ክረምት የሚተከሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በስፋት እየተዘጋጁ ነው

ነቀምቴ፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦በምሥራቅ ወለጋ ዞን በመጪው ክረምት የሚተከሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በስፋት እየተዘጋጁ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በጽሕፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ቡድን መሪ አቶ ደሳለኝ በለጠ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በስፋት እየተዘጋጁ ነው።


 

በዘንድሮው መርሐ ግብር ለሁሉም የችግኝ ዓይነቶች ትኩረት ቢሰጥም፣ ይበልጥ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ዝርያዎች ላይ ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት። 

እየፈሉ ከሚገኙት ችግኞች መካከል አትክልትና ፍራፍሬ፣ የደንና ጥምር ደን ዝርያዎች፣ ቀርከሃ፣ የእንስሳት መኖ  የሚገኙበት መሆኑን ነው የተናገሩት።

የእጽዋት ስብጥሩ ከአካባቢው አየር ንብረት ጋር የሚስማማና በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ካለፉት ዓመታት ተሞክሮ በመነሳት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የጉድጓድ ዝግጅት መጀመሩን የጠቆሙት አቶ ደሳለኝ፤ የአየር ንብረት ጥናት፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም የሕብረተሰቡን ተሳትፎ የሚያሳድጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዘንድሮው ተከላ የሚውል 107 ሺህ ሄክታር መሬት የተዘጋጀ ሲሆን፣ በዞኑ በሚገኙ 2 ሺህ 194 የመንግሥትና የግል የችግኝ ጣቢያዎችም የችግኝ እንክብካቤ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ችግኝ መትከል ከመደበኛ መርሐ ግብር ባለፈ የሥራ ባሕላቸው እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ።


 

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ወይዘሮ አዲስዓለም በለጠ ባለፉት ዓመታት በተተከሉ ችግኞች በአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ለውጥ መታየቱን ገልጸዋል። 

አቶ ተሰማ መኮንንም በተመሳሳይ ቀደም ሲል ለደን የነበረው ዝቅተኛ አመለካከት ተቀይሮ፣ ዛሬ ሕብረተሰቡ የተራቆቱ ቦታዎችን መልሶ በማልማትና በመንከባከብ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 


 

ለዘንድሮው ተከላም አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም