በሐረሪ ክልል ከ357 ሺህ በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ወስደዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል ከ357 ሺህ በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ወስደዋል
ሐረር፤ ሚያዝያ 15/2018(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል ከ357 ሺህ በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መውሰዳቸውን የክልሉ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ገለጸ።
የሐረሪ ክልል ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ሃላፊና የክልሉ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አስተባባሪ ሳዳም መሐመድ እንደገለጹት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን በክልሉ የከተማና ገጠር ወረዳዎች ተደራሽ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ነው።
በዚህም ባለፉት 9 ወራት ብቻ ከ180 ሺህ በላይ ዜጎች መታወቂያውን መውሰዳቸውንና በአጠቃላይ በእስካሁኑ ሂደት ከ357 ሺህ በላይ ዜጎች መታወቂያውን መውሰዳቸውን ጠቅሰዋል።
ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሳካት ጉልህ አበርክቶ አለው ሲሉም ገልጸዋል።
በተለይም የዲጂታል ማንነት መለያ ተቋማት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ በማስቻል ግልፅነትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
መታወቂያው በአገልግሎት ሰጪና ተቀባዩ መካከል ይበልጥ መተማመን እንዲኖር የሚያስችል፣ የተቋማትን ሥራ የሚያቀናጅ፣ በግለሰቦች ደረጃም የራስን መብት የሚያስጠብቅ መሆኑንም አክለዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ምዝገባ ያላካሄዱ የማህበረሰብ ክፍሎችም በአቅራቢያቸው በሚገኙ የምዝገባ ማዕከላት አገልግሎቱን እንዲጠቀሙ ሃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።