ቀጥታ፡

ማንችስተር ሲቲ የሊጉን መሪነት ከአርሰናል ተረከበ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2018 (ኢዜአ):- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 34ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ማንችስተር ሲቲ በርንሌይን 1 ለ 0 አሸንፏል።

 

በተርፍ ሙር ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አርሊንግ ሃላንድ በአምስተኛው ደቂቃ የማሸነፊያ ግቧን አስቆጥሯል።

በጨዋታው ማንችስተር ሲቲ ከፍተኛ ብልጫ ቢወስድም ያገኛቸውን ግልጽ የግብ እድሎች መጠቀም አልቻለም።

ባለሜዳው በርንሌይ በጥልቀት የመከላከል እና የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴን አድርጓል።

በሊጉ 21ኛ ድሉን ያስመዘገበው ማንችስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ70 ነጥብ የሊጉን መሪነት ከአርሰናል ተረክቧል።

ሁለቱም ክለቦች በተመሳሳይ 70 ነጥብ እና 37 የግብ ክፍያ ቢኖራቸውም ማንችስተር ሲቲ ባስቆጠረው የጎል ብዛት (66) የሊጉ መሪ ሆኗል።

አርሰናል ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል።

የሲቲ ማሸነፍ የሊጉን የዋንጫ ፉክክር ይበልጥ አጓጊ አድርጎታል።

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 22ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው በርንሌይ በ20 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

በርንሌይ አራት ጨዋታዎች እየቀሩት ከፕሪሚየር ሊግ መውረዱ ተረጋግጧል።

ዎልቭስ ከሊጉ አስቀድሞ መውረዱ የተረጋገጠ ክለብ ነው።

 

በሌላኛው መርሐ ግብር ቦርንማውዝ እና ሊድስ ዩናይትድ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።

በቫይታሊቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጁኒየር ክሩፒ  እና ራያን ግቦቹን ለቦርንማውዝ አስቆጥረዋል።

ሲን ሎንግስታፍ እና የቦርንማውዙ ጀምስ ሂል በራሱ ላይ ለሊድስ ዩናይትድ ብቸኛውን ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ቦርንማውዝ በ49 ነጥብ ደረጃውን ከዘጠነኛ ወደ ሰባተኛ ከፍ አድርጓል።

ባለፉት 14 የሊጉ ጨዋታዎች ያልተሸነፈው ቦርንማውዝ በጠንካራ ግስጋሴ ላይ ይገኛል።

ሊድስ ዩናይትድ በ40 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ወሳኝ አንድ ነጥብ አግኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም