ቼልሲ ሊያም ሮሲኒየርን አሰናበተ - ኢዜአ አማርኛ
ቼልሲ ሊያም ሮሲኒየርን አሰናበተ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፦ የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ዋና አሰልጣኙን ሊያም ሮሲኒየርን ከኃላፊነት ማሰናበቱን በይፋ አስታውቋል።
አሰልጣኙ በስታምፎርድ ብሪጅ በነበራቸው ቆይታ ክለቡን መምራት የቻሉት ለአራት ወራት ብቻ ሲሆን፣ ይህ ውሳኔ የተላለፈው ቡድኑ እያሳየ ባለው እጅግ ደካማ ውጤት ምክንያት መሆኑን ቢቢሲ ክለቡን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
በሮሲኒየር መሪነት ቼልሲ ካለፉት ዘጠኝ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአንዱ ብቻ ሲሆን፣ በተለይም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ቡድኑ ምንም አይነት ግብ ሳያስቆጥር መሸነፉ ለአመራሮቹ ትዕግስት ማጣት ዋነኛ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።
ቼልሲ ትናንት በሊጉ በብራይተን 3 ለ 0 መሸነፉ ይታወቃል።
ሮሲኒየር የስድስት ዓመት ተኩል ረጅም ኮንትራት ፈርመው ወደ ክለቡ ቢመጡም፣ ቼልሲን በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ ሰባተኛ ደረጃ ዝቅ ማድረጋቸው እና የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ እድላቸውን አደጋ ላይ መጣላቸው ለስንብቱ ምክንያት ሆኗል።
ክለቡ ለሮሲኒየር እና ለረዳቶቻቸው በቆይታቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናውን አቅርቧል።
በመጪው እሁድ ቼልሲ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ለሚያደርገው የኤፍ ኤ ካፕ (FA Cup) የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ፣ ካሉም ማክፋርሌን
ቡድኑን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት እንደሚመሩ ክለቡ አስታውቋል።
ቼልሲ በአሁኑ ወቅት ቋሚ አሰልጣኝ ለመቅጠር ጥረት እያደረገ ሲሆን፣ ይህም በባለቤቱ ቶድ ቦህሊ ዘመን አምስተኛው አሰልጣኝ እንደሚሆን ቢቢሲ ዘግቧል።