ቀጥታ፡

በተተገበሩ የሪፎርም ስራዎች የግብርና ዘርፉን ወደ ሜካናይዜሽን ማሸጋገር ያስቻሉ ተጨባጭ ወጤቶች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡- ባለፉት የለውጥ ዓመታት በኢትዮጵያ የተተገበሩ የሪፎርም ስራዎች የግብርና ዘርፉን ወደ ሜካናይዜሽን ማሸጋገር ያስቻሉ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።

የ2018 በጀት ዓመት ሦስተኛው የመቶ ቀናት እና የዘጠኝ ወራት ስራ አፈጻጸም ሪፖርት  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል።

የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በሰጡት ማብራሪያ፣ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተተገበሩ የሪፎርም ስራዎች የግብርና ዘርፉን ወደ ሜካናይዜሽን ማሸጋገር የሚያስችሉ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልፀዋል።

በዚህም አጠቃላይ ኢኮኖሚው ወደ ፊት እንዲራመድ፣ ፈጣንንና ጥራት ያለው ኢኮኖሚ እንዲመዘገብ በማስቻል ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ እድገት መመዝገቡን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም ዝቅተኛ የግብርና ማሽነሪ ቁጥር ለማሳደግ መንግሥት የፖሊሲ ማበረታቻ በማድረግ አርሶ አደሮቹ ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ እና የብድር አቅርቦት በማመቻቸት ሰፊ ስራ መሰራቱን አንስተዋል።

በዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተሰራው ስራ ወደ 27 ሺህ ትራክተሮች ከ8 ሺህ በላይ ኮምባይነሮች እንዲሁም ከ280 ሺህ በላይ በሞተር የሚሰሩ ፓምፖች ተደራሽ ማድርግ መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም የግብርናው ስራ ከዝማላዳዊ አሰራር ተላቆ ወደ ሜካናይዜሽን እየተሸጋገረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፉት አመታት በተሰራ ስራ የሜካናይዜሽን እድገቱ 72 በመቶ መድረሱን ያሳያል ነው ያሉት።  

አጠቃላይ በኢትዮጵያ በትራክተር የሚለማ መሬት 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት የደረሰ ሲሆን ይህ ማለት ከሚለማው መሬት አንድ ሶስተኛውን በትራክተር ማልማት እንደተቻለ ገልፀዋል።

ይህም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለገበያ የሚቀርበውን ምርት በማሳደግ የአርሶ አደሩን ህይወት በመቀየር ረገድ ትልቅ ለውጥ ማስመዝገቡን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ባለፉት የለውጥ አመታት ተግባራዊ የተደረገው ሪፎርም የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ወደ መስኖ ለማሸጋገር በተደረገው ጥረት የመስኖ ልማት ሽፋኑ ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መጥቷል ነው ያሉት።

በዘንድሮው ዓመት ብቻ 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ወደ 3 ነጥብ 87 ሚሊየን ሄክታር ማልማት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ይህም አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ በዓመት ሁለትና ከዚያ በላይ እንዲያመርት በማድረግ እንደ ሀገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ተጨባጭ ለውጥ ማሳየቱን ተናግረዋል። በተጨማሪም ለዜጎች ሰፋፊ የስራ እድል እየፈጠረ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ከምግብነት ባለፈ በመጠንም በጥራትም ተወዳዳሪ ምርቶችን በማምረት ለዓለም ገበያ ተደራሽ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም