ቀጥታ፡

አትሌት ገመኔ ማሚቴ ምትኩ በተከለከለ አበረታች ቅመም ምክንያት የስድስት ዓመት እገዳ ተጣለባት 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን አትሌት ገመኔ ማሚቴ ቱኩ የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን (Doping) ተጠቅማ በመገኘቷ የስድስት ዓመት የእገዳ ቅጣት እንደተጣለባት አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በሁለት የተለያዩ ውድድሮች ላይ ባካሄዳቸው ምርመራዎች፣ አትሌቷ ኤሪትሮፖይቲን (EPO) እና ዴክሳሜታሶን (Dexamethasone) የተባሉ የተከለከሉ ንጥረ ነገሮችን መጠቀምዋን ማረጋገጡን አመልክቷል። 

በዚህም መሠረት አትሌት ገመኔ ማሚቴ ቱኩ ጊዜያዊ እገዳ ከተጣለባት ጥቅምት 2 ቀን 2018 ዓ.ም (November 11, 2025) ጀምሮ ለስድስት  ዓመታት የሚጸና፣ በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር እንዳትሳተፍ እገዳ መጣሉን ገልጿል። 

በተጨማሪም አትሌቷ ከግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም (May 11, 2025) ጀምሮ በተካሄዱ የተለያዩ ውድድሮች ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች በሙሉ እንዲሰረዙ ተወስኗል።

ይህም ሜዳሊያዎችን፣ የማዕረግ ስሞችን፣ ደረጃዎችን እና የሽልማት ገንዘቦችን መመለስን እንደሚጨምር ነው ባለስልጣኑ ያስታወቀው። 

በቀጣይም በሀገሪቱ በየደረጃው የሚደረገው የምርመራና ቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል። 

የኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመጠቀምም ሆነ በተለያየ መልኩ የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰት በሚፈጽሙ አትሌቶችና ከጀርባ ሆነው በሚያበረታቱ ሌሎች ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው የእርምት እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም