ቀጥታ፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት 4 ነጥብ 85 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 4 ነጥብ 85 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለዘርፉ ትልቅ መሰረት መጣሉን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን 754 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መግባታቸውን ጠቁመዋል።

የ2018 በጀት ዓመት ሦስተኛው የመቶ ቀናት እና የዘጠኝ ወራት ስራ አፈጻጸም ሪፖርት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  በተገኙበት  ተገምግሟል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በሰጡት ማብራሪያ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን በማሳካት ረገድ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

የሪፎርም ሥራዎቹ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር እንዲሁም የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል ስኬታማ መሆናቸውን አንስተዋል።

ቀደም ሲል 4 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ የነበረው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዕድገት አሁን ላይ በሁለት አሃዝ አድጎ ከ13 በመቶ በላይ ደርሷል ነው ያሉት።

የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ገቢ ምርትን በመተካትና በወጪ ንግድ ዘርፍ  አመርቂ ለውጥ ማምጣታቸውን ጠቁመዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 433 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የኢንዱስትሪ ምርቶች ለውጭ ገበያ የቀረቡ ሲሆን የዘርፉ የኃይል አጠቃቀምም ማደጉን ተናግረዋል።

የገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተሠራው ሥራ 4 ነጥብ 85 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ማምረት መቻሉን አስታውቀዋል።

ይህ ውጤት የኑሮ ጫናን በማቅለል እና የኢኮኖሚ መነቃቃትን በማምጣት ረገድ ትልቅ ሚና መጫወቱን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለዘርፉ ትልቅ መሰረት መጣሉን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን 754 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መግባታቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይም የምርት አቅምን ለማሳደግ የፋይናንስ፣ የግብዓት፣ የኃይል አቅርቦት እና ምቹ የገበያ ሁኔታዎችን በመፍጠር ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም