የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የቴክኖሎጂ ዳኝነት አገልግሎቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የቴክኖሎጂ ዳኝነት አገልግሎቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡- የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የቴክኖሎጂ ዳኝነት አገልግሎቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸምን ገምግሟል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፤ የፍርድ ቤቶችን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃጸም ዝርዝር ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።
በሪፖርታቸው የኢትዮጵያን የዳኝነት አገልግሎት ለማዘመን የተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በዲጂታል ክስ መስተንግዶ፣ በተዘዋዋሪ ችሎትና የቆዩ መዝገቦችን በማጥራት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትርጉም ያለው ስኬት መገኘቱን ተናግረዋል።
የሰው ሃብት ልማት ተግባራትም የዳኞችንና የሕግ ሙያተኞችን አቅም በማጎልበት በመዝገብ ክምችት ቅነሳ፣ በጊዜ ቀጠሮና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ እየዳበረ መምጣቱን አንስተዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዘጠኝ ወራት ዝርዝር የአፈፃጸም ሪፖርት ዙሪያ ምላሽ የሚሹ ጥያቄና አስተያየቶችን አቅርበዋል።
በአርዓያነት የሚወሰደውን የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዲጂታል ዳኝነት አገልግሎት በክልል ፍርድ ቤቶች ጭምር ለማስፋት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
የዳኝነት አገልግሎቱን ለማሳለጥ ተግባራዊ የተደረገው ቴክኖሎጂ ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አኳያ ስላመጣው እምርታ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በምላሻቸው፤ ዲጂታል የዳኝነት የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት ወሳኝ መፍትሔ ሆኖ እያገለገለ ነው።
አክለውም ተግባራዊ እየሆነ ያለው ዲጂታላይዜሽን ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት ተግባራዊ እንዲሆን ማስቻሉን ነው የተናገሩት፡፡
በቀጣይም የዳኝነት ሥርዓቱን የሚያሳልጡ አገልግሎቶችን የበለጠ በማስፋት በክልሎች ጭምር የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ በሰጡት ማጠቃለያ፤ የፌዴራል ፍርድ ቤት የሥራ አፈፃጸም በሪፖርትና በመስክ ምልከታ መታየቱን ገልጸዋል።
በመስክ ምልከታና ሪፖርቱም የፍርድ ቤቶች ፈጣንና ጥራት ያለው የቴክኖሎጂ የዳኝነት አገልግሎት ውጤታማነትን በማሳደግ በአርዓያነት የሚወሰዱ መሆናቸውን አረጋግጠናል ብለዋል።
በቀጣይም ዘመናዊና ግልፅ የዳኝነት ምኅዳርን በማስፋት የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።