የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሪፎርም በፓርቲዎች መካከል የትብብርና የፉክክር ሚዛን ማስጠበቅ ያስቻለ ምኅዳር ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሪፎርም በፓርቲዎች መካከል የትብብርና የፉክክር ሚዛን ማስጠበቅ ያስቻለ ምኅዳር ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሪፎርም በፓርቲዎች መካከል የትብብርና የፉክክር ሚዛን ማስጠበቅ ያስቻለ ምኅዳር መፍጠሩን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
የ2018 በጀት ዓመት ሦስተኛው የመቶ ቀናት እና የዘጠኝ ወራት ስራ አፈጻጸም ሪፖርት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በሰጡት ማብራሪያ፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች የተወሰዱ የሪፎርም እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤቶች አስገኝተዋል ብለዋል።
በዚህም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተወሰዱ የሪፎርም እርምጃዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ በመፈጸም ተጠባቂ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማድረጉን ገልጸዋል።
ይህም የኢትዮጵያና ህዝቦቿን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እመርታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ ማስቻሉንም ተናግረዋል።
ገዥው ፓርቲ በፖለቲካው መስክ የወሰዳቸው የሪፎርም እርምጃዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የትብብርና ፉክክር ሚዛንን ማስጠበቅ ያስቻለ ምኅዳር መፍጠሩን አስረድተዋል።
በዚህም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር የሚሰሩበትን ጤናማ የፉክክር መድረክ መፈጠሩን አንስተዋል።
ገዥው ፓርቲም በየደረጃው የሥራ ኃላፊዎችን የመመደብ ሥልጣንና ኃላፊነት እንዳለው አስታውሰው፤ የትብብርና የሃሳብ ልዕልና ባህልን ለማዳበር የኢትዮጵያን የመግባባት ዴሞክራሲን ማጠናከር የሚያስችል የተሳትፎ ምኅዳር መፍጠሩን ገልጸዋል።
ከፌዴራል እስከ ወረዳ በሚገኙ የመንግስት መዋቅሮችም ከ275 በላይ የሚሆኑ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተመድበው ህዝባቸውንና ሀገራቸውን እያገለገሉ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሪፎርም በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትና አንድነትን ለመፍጠር አካታች ሀገራዊ ምክክሩ የተሻለ የምክክር ምዕራፍ ላይ መድረሱንም ጠቁመዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሪፎርም ውጤታማነትን በማስቀጠል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለመፍጠር የተጀመሩ ጥረቶች የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አቶ አደም አረጋግጠዋል።
መንግስትና ገዥው ፓርቲም መርህን በጠበቀ መልኩ ሀገራዊ ምክክሩ በህዝብና ባለድርሻ አካላት የላቀ ተሳትፎ ግቡን እንዲመታ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በሌላ መልኩ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ሌሎች ሀገራት በአርዓያነት የሚወስዱት ተጨባጭ ውጤቶች እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም የኢትዮጵያ ብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት የሀገር ውስጥ ፍጆታን በማሟላት የዓለም አቀፍ ወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ የሚያስችል ስኬት ማስገኘቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተኪ ምርት እንዲመረት እና የተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ እመርታዊ ውጤት ማስገኘቱን ጠቅሰዋል።
በማህበራዊ ዘርፍም ፍትሕዊ የመሰረተ ልማት ተደራሽነቶች ጥራትና አካታችነትን በማስጠበቅ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደጉን አስገንዝበዋል።
በተለይም የትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር የቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት የትምህርት ጥራትን የሚያስጠብቅ ውጤት እየተገኘበት መሆኑን አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና በዲፕሎማሲው መስክ የኢትዮጵያና ህዝቦቿን ክብር በማስጠበቅ ሁለንተናዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጡ የልማት ድሎች መገኘታቸውን አብራርተዋል።
በቀጣይም የመንግስት፣ የግሉ ዘርፍና የህዝብን ተሳትፎና አቅሞችን በመደመር ሁለንተናዊ ብልፅግና፣ የዳበረ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ዘላቂና አዎንታዊ ሰላም ባለቤት ኢትዮጵያን መገንባት ይጠበቅብናል ብለዋል።