ቀጥታ፡

የክልል የሕዝብና የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ሀገራዊ አጀንዳዎችን ተደራሽ እያደረጉ ነው

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡- የክልል የሕዝብና የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ለሀገራዊ መግባባትና ትርክት ግንባታ መሰረት የሚሆኑ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ገንቢ ሚና እየተወጡ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ባለፉት ሶስት ወራት በክልል የሕዝብ እና የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን ላይ ያደረገውን የይዘት ስርጭት ክትትልና ግምገማ ውጤት ይፋ ማድረጊያ መርሃ ግብር  "መገናኛ ብዙሃን ለሀገር ግንባታና ለማህበረሰብ አመለካከት ቀረፃ" በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል፡፡


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በመገናኛ ብዙሃን ላይ አበረታች ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ ነው።

የክልልና የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን የህዝብን ፍላጎትንና ችግሮችን በቅርበት በመለየት ተደራሽ ማድረግ የሚችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በክልሎች ማህበረሰቡን በሚያወያይበት ወቅት ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ በማድረግ የጎላ አበርክቶ እንደነበራቸውም ተናግረዋል።

እነዚህ የክልል የሕዝብና የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን እውነተኛ የኢትዮጵያን ብዝሃነት ስዕል የምናይባቸው ተቋማት ናቸው ብለዋል።

የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ያላቸውን አቅም አሟጠው በመጠቀም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መልካም ጥረት እያደረጉ ነው ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ የክልል የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን አቅማቸውን የሚያጠናክሩበት ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልል የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ወጥ ዘገባ በመስራት ብሔራዊ መግባባት ላይ የጋራ አቋም መያዝ መጀመራቸውን የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ አስተሳሳሪ ትርክት ለመገንባት በቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተናብበው እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡

በድህረ እውነት ዘመን የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ፈታኝ በመሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ቁልፍ ሥራ እውነትን ፈልጎ ማውጣት መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራልና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ በክልል የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን መካከል የዜና እና የተሞክሮ ልውውጥ ማድረግ ከተቻለ ኢትዮጵያን በጋራ እንገነባለን ብለዋል፡፡


 

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ሲባል ማን ሰራ ሳይሆን እንዴት በጋራ እንቋደሰዋለን የሚለው ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፤ የክልል ሥራዎችን በትብብር በመስራት ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ፤ የክልል መገናኛ ብዙሃን ከክልል አጥር በመውጣት በተለያዩ ቋንቋዎች የተለያዩ ይዘቶችን ማሰራጨት መቻላቸው ትልቅ ለውጥ መሆኑን አንስተዋል፡፡


 

ይሁን እንጂ የክልል የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን በጋራ ታሪክ፣ በአስተሳሳሪ ጉዳዮችና በጋራ እሴት ግንባታ ላይ ከዚህ በላይ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ አሁን ያለንበት የድህረ እውነት ዘመን እውነት የቀጨጨችበትና በብዙ የምትፈተንበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በመሆኑም የክልል የህዝብና የማህበረሰብ የመገናኛ ብዙሃን እውነትን ለማጽናት ደጋግመውና በተለያየ ሥልት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ የመገናኛ ብዙሃን ተወካዮች በበኩላቸው፤ የክልል የህዝብና የማህበረሰብ የመገናኛ ብዙሃን የለውጡ አካል ተደርገው የብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ መግባባት ላይ ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡


 

ሀገራዊ አጀንዳዎችን እንዲጋሩ፣ የአጀንዳዎቹ ባለቤቶች እንዲሆኑ መደረጉን በማንሳት፤ ይሄውም በጋራ እንዲቆሙ አስችሏቸዋል ብለዋል፡፡

የክልል የህዝብና የማህበረሰብ የመገናኛ ብዙሃን በሰው ሀይልም ሆነ በቴክኖሎጂ የአቅም ልዩነት ስላላቸው ሁሉም ፈጣን መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ እንዲችሉ  መተጋገዝ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም