ቀጥታ፡

በክልሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አካባቢ መፍጠር ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ ነው

ሀዋሳ ፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል ዘመናዊና ቀልጣፋ አሰራሮችን በመዘርጋት በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ክልሉ በመሳብ የዜጎችን  ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ አተገባበር ስልትን በተመለከተ ለተለያዩ አካላት በሃዋሳ ከተማ የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠና እየሰጠ ነው።


 

የቢሮው ሀላፊ አቶ አሻግሬ ጀንበሬ በስልጠናው ላይ እንደገለጹት፣ በክልሉ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የማምረት አቅምን ለማጎልበት በተቀናጀ መንገድ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የተዘረጉ የተለያዩ የድጋፍና ክትትል ሥራዎች በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይም በክልሉ በግብርና ምርቶች ማቀነባበር፣ በማዕድን ልማትና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች የወጪና ተኪ ምርት በማምረት ተልዕኳቸውን እየተወጡ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

ኢንዱስትሪዎቹ ለኢኮኖሚው መነቃቃት ካላቸው ጠቀሜታ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ለዜጎች ተጠቃሚነት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም አስረድተዋል።

በቀጣይም ዘመናዊና ቀልጣፋ አሰራሮችን በማጠናከር በርካታ ኢንዱስትሪዎችን ለመሳብና የዜጎችን ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

እንደ አቶ አሻግሬ ገለጻ፤ በክልሉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ተከትሎ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው የነበሩ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ወደሥራ እንዲገቡ ተደርገዋል።

በዚህም በክልሉ 44 በመቶ የነበረው የኢንዱስትሪ የማምረት አቅም ወደ 65 በመቶ ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል። 

የስልጠናው ዓላማም ፖሊሲውን ወጥ በሆነና በተቀናጀ መልኩ በመተግበር ለኢንዱስትሪዎች የሚደረገውን ድጋፍ ማጠናከርና ውጤታማነትን ማሳደግ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከሰልጣኞች መካከል የደቡባዊ እና የማዕከላዊ ሲዳማ ዞኖች የኢኮኖሚ ልማት መምሪያ የኢንዱስትሪ ልማት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ደበላ እና አቶ ዮሴፍ ብርሀኑ እንዳሉት ስልጠናው ዘርፉን በአግባቡ ለመደገፍና እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ለማጠናከር ጠቀሜታው የጎላ ነው።


 

በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተገኘውን ውጤት የዘርፉን ወሳኝነት ያረጋገጠ መሆኑን ጠቁመው፣ ኢንዱስትሪዎችን በተቀናጀ መልኩ በመደገፍ ውጤቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንሰራለን ብለዋል።

በስልጠናው ከክልል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ደጋፊ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም