የኢትዮጵያን የተጽዕኖና የትብብር አድማስ ያሳደጉ ስትራቴጂካዊ የዲፕሎማሲ ስኬቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የተጽዕኖና የትብብር አድማስ ያሳደጉ ስትራቴጂካዊ የዲፕሎማሲ ስኬቶች ተመዝግበዋል
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡- ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኢትዮጵያን የተጽዕኖና የትብብር አድማስ ያሳደጉ ስትራቴጂካዊ የዲፕሎማሲ ስኬቶች መመዝገባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለፁ።
በኢኮኖሚ፣ በተቋም ግንባታና በአካባቢ የተከናወኑ ተግባራትም ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት የጀርባ አጥንት መሆናቸውን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የ2018 በጀት ዓመት ሦስተኛው የመቶ ቀናት እና የዘጠኝ ወራት ስራ አፈጻጸም ሪፖርት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) በዲፕሎማሲ መስክ የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት አበረታች የዲፕሎማሲ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተጽዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን አስታወቀዋል።
የኢትዮጵያን አንኳር ስትራቴጂካዊ ፍላጎት የሆነው የባህር በር አጀንዳ በዓለም አቀፍ መድረኮችና በሁለትዮሽ ግንኙነቶች ትልቅ ትኩረት እንዲያገኝ ተደርጓል ብለዋል።
ይህም የተለያዩ አካላት የኢትዮጵያን ጥያቄ እንዲገነዘቡና ለጉዳዩ በጋራ መፍትሔ መፈለግ አስፈላጊ መሆኑን እንዲረዱ በማድረግ ረገድ ትልቅ ድል መገኘቱን ገልጸዋል።
ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጫናዎች ቢኖሩም፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ ጫናዎቹን በመቋቋም የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ ማድረግ መቻሉ ሌላኛው ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ ሙሉ አባል ሀገር ሆና መመረጧና ንቁ ተሳትፎ መጀመሯ የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የሚያሳይ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንትና ለኢኮኖሚ አጋርነት ያላት ተፈላጊነት እየጨመረ መምጣቱንም ጠቅሰዋል።
የቅርብና የሩቅ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
የከፍተኛ አመራሮች የጉብኝት ልውውጦችና የሚፈረሙ ስምምነቶች የኢትዮጵያ የትብብር አድማስ መስፋቱን የሚያሳዩ ተጨባጭ ውጤቶች ናቸው ብለዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የውሳኔ ሰጪ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ድምፅ ስትመረጥ መቆየቷን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
በተለይም በግለሰብ ደረጃ የሚወከሉ የኢትዮጵያ እጩዎች በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ መሆናቸው የሀገሪቱ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እያደገ መምጣቱን የሚያረጋግጥ እንደሆነ ገልፀዋል።
የዲፕሎማሲ ስኬቱ በተጨባጭ የሀገር ውስጥ ስራዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አብራርተዋል።
የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የሀገሪቱን ተቋማት በማጠናከር ለውጤት የበቁ አቅሞች እንዲሆኑ ማስቻሉንም አንስተዋል።
በአካባቢ ጥበቃና በታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት የተሰሩ ስራዎች ለሌሎች ሀገራት እንደ ተምሳሌት እየታዩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
የከተማና የገጠር ልማት እንቅስቃሴዎች ተደምረው ኢትዮጵያ ለትብብርና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን አድርገዋታል ብለዋል።
በኢኮኖሚ፣ በተቋም ግንባታና በአካባቢ ጥበቃ የተከናወኑ ተግባራት ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት የጀርባ አጥንት መሆናቸውንም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።