በድሬዳዋ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 84 የተዘጉና በግንባታ ላይ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ተሸጋግረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 84 የተዘጉና በግንባታ ላይ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ተሸጋግረዋል
ድሬዳዋ፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡- በድሬዳዋ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 84 የተዘጉና በግንባታ ላይ የነበሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን የአስተዳደሩ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለፀ።
በአስተዳደሩ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ እየተመዘገቡ የሚገኙ ውጤቶችን የሚያሳይ "ድሬ ታምርት፤ ኢትዮጵያ ትበልፅግ" በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ የኢንዱስትሪ ኤክስፖ ነገ ይጀመራል።
ኤክስፖውን አስመልክተው የአስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡስማን አህመድ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ ኡስማን እንደገለጹት፤ ባለፉት አራት ዓመታት በተካሄደው እና ዘንድሮም በቀጠለው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ተዘግተውና በግንባታ ላይ የነበሩ 84 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ተሸጋግረዋል።
በንቅናቄው በተደረጉ ልዩ ድጋፍ እና ክትትሎች የመካከለኛ እና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የፋይናንስ፣ የመሬት፣ የመሠረተ ልማት፣ የኤሌክትሪክ እና የሌሎች አገልግሎት ጥያቄዎች በተቀናጀ መልኩ መፈታታቸውን አንስተዋል።
ከ34 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡት እነዚሁ ኢንዱስትሪዎች 87 ዓይነት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በራስ አቅም በማምረት የውጭ ምንዛሬን እያስቀሩ ይገኛሉ ብለዋል።
ከ17 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸውንም አንስተዋል።
ለአራተኛ ጊዜ የተዘጋጀው እና ነገ በይፋ በሚጀመረው ኤክስፖው ላይ 50 አምራች ኢንዱስትሪዎች የተለያዩ ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ የገበያ፣ የግብአትና የእርስ በርስ መመጋገብ እና ትስስር እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።
ለአንድ ሳምንት በሚዘልቀው ኤክስፖው ላይ የፌደራልና የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ የዘርፉ አመራሮች እንደሚሳተፉም ይጠበቃል።