ቀጥታ፡

ረቂቅ አዋጁ የወጪና የገቢ ንግድን ለማሳለጥ የጎላ አስተዋፅኦ ይኖረዋል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡-የጉምሩክ አዋጅ ረቂቅ ማሻሻያ የወጪና የገቢ ንግድን ለማሳለጥ የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጉምሩክ አዋጅ ረቂቅ ማሻሻያ ላይ የህዝብ ይፋዊ ውይይት አድርጓል።


 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጀ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ረቂቅ አዋጁ ሀገራዊ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እንዲሁም ከዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ድንጋጌዎች ጋር የተናበበ ለማድረግና የጉምሩክን አሰራር ለማዘመን የተደረገ ማሻሻያ ነው። 

የጉምሩክ አሰራር ላይ እንቅፋት የፈጠሩ ድንጋጌዎችን በማሻሻል በወጪና የገቢ ንግድን ለማሳለጥ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።


 

ዘርፉን በማዘመን የጉምሩክ ስርዓቱ ዓለም ከደረሰበት የአሰራር ስርዓት ጋር የበለጠ እንዲጣጣም ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፤ ማሻሻያው አስፈላጊ እና በትክክለኛ ጊዜ የተደረገ ነው ብለዋል።


 

በረቂቅ አዋጁ የተካተቱት ማሻሻያዎች ኮንትሮባንድን እና ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አዘዘው ጫኔ በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ሁኔታ ውስጥ ጠንካራ የጉምሩክ ሥርዓት መዘርጋት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። 


 

በተጨማሪም ማሻሻያው ምቹ የንግድ እንቅስቃሴን ለመፍጠርና የንግድ ሥርዓቱ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲካሄድ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የህግ ባለሙያ አቶ አብርሃም ረጋ በበኩላቸው፤ አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ጋር ለማጣጣም እና ለሀገር ወስጥ ኢንዱስትሪ ከለላ ለመስጠት እንደሆነ ተናግረዋል።


 

በተጨማሪም ህገ ወጥ ንግድ መከላከል፣ የድንበር ጥበቃ፣ ከዓለም አቀፍ የንግድ ስምምነት ጋር ለማጣጣም፣ ድንበርን ለመጠበቅ፣ የስታቲስቲክስ መረጃን ለመያዝ እንዲሁም ሕጋዊ ንግድንና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እንደሆነም ገልጸዋል።

በአዋጁ ላይ 22 የሚሆኑ አንቀፆች ማሻሻያ እንደተደረገባቸው በዚሁ ጊዜ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም