ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ቁልፍ ሚና ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2018(ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ዜጎች የመንግሥትን አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኙ በማድረግ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎትን አስጀምረዋል።

በዚሁ ወቅት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ለመንግሥት አገልግሎት መሳለጥ ወሳኝ መሰረት ጥሏል ብለዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም በቅርቡ ወደ ስራ በማስገባት የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እያሳለጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት የሚሰጡ የመንግሥት አገልግሎቶች የዜጎች እንግልት ምንጭ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ለዚህም ከዓመት ወዲህ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስጀመር ዜጎች የመንግሥት አገልግሎቶችን ፈጣን፣ ዘመናዊና ግልፅ በሆነ አሰራር እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።

የዲጂታል እመርታ መንግሥት የአገልግሎት ቅልጥፍና መገለጫ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ዜጎች በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ የሚያገኙበትን ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

ይህም እንግልትን በማስቀረት የመንግሥትን የሥራ ሂደት በማፋጠን የተሻለ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስረድተዋል።

ለአብነትም የዲጂታል መታወቂያን ጨምሮ የተበታተኑ የመንግሥት አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል መሰጠት ሲችሉ ከፍተኛ ሀገራዊ ፋይዳ እንዳላቸው አብራርተዋል።


 

በአዲስ አበባ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሎች ጭምር የተደራሽነት አድማሱን በማስፋት ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ዕቅድ መነሻነት የተገኘውን እመርታ በማስፋት የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን አቅም ለመገንባት መትጋት ይጠይቃል ብለዋል።

የአዲስ አበባ መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት መንግሥት አገልግሎቶችን ወደ ዜጎቹ ለማቅረብ ታስቦ ሥራ ላይ የዋለ ወሳኝ እርምጃ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህም ዜጎች ባሉበት ቦታ የሚቀርብላቸውን የመንግሥት አገልግሎቶች በጥራት እንዲያገኙ በማስቻል ዲጂታል ኢኮኖሚና ሀገር ለመገንባት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም