ቀጥታ፡

በያዝነው ካርድ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀም የምርጫውን ዕለት እየጠበቅን ነው

ሀዋሳ/ቦንጋ ፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡- በያዝነው ካርድ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀም የምርጫውን ዕለት እየጠበቅን እንገኛለን ሲሉ የሀዋሳና የቦንጋ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ።

በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባ ዛሬ ይጠናቀቃል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሃዋሳና የቦንጋ ከተሞች ነዋሪዎች ፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በያዝነው ካርድ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀም የምርጫውን ዕለት እየጠበቅን እንገኛለን ብለዋል።

አቶ አሸናፊ አለሙ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ፣ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣትና ይበጀኛል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ በመውሰድ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ምርጫ ቦርድ ያመቻቸው ተጨማሪ የምዝገባ ቀን በስራ መደራረብ ምክንያት ጊዜ ላላገኙ ዜጎች መልካም እድልን የፈጠረ በመሆኑ ካርድ ለመውሰድ አስችሎኛል ነው ያሉት፡፡

በምርጫው ንቁ ተሳታፊ ለመሆን የምርጫ ካርድ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን በማመን በመጨረሻው ቀን ካርድ ወስጃለሁ የሚሉት ደግሞ  የከተማዋ ነዋሪ አቶ ታረቀኝ ድቃሶ ናቸው፡፡


 

ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ለሀገር የሚጠቅም ፓርቲን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረው የፓርቲዎቹን የምረጡኝ ቅስቀሳ እየተከታተሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ሙሴ ኤልያስ በበኩላቸው፤ በተመቻቸላቸው ቀን ተጠቅመው የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረው ለሀገር ልማት ይጠቅማል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው ፤ለጠቅላላ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም የሚያስችላቸውን ካርድ በመያዝ ድምጽ የመስጫ ቀኑን እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በከተማው 03 ሸታ ምርጫ ጣቢያ ካርድ ሲወስዱ ያነጋገርናቸው የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ተማሪዎች መቅደስ መኮንን እና መሠለች ወንድሙ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ለመሳተፍ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

በመጨረሻ ቀንም ቢሆን ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም የሚያስችላቸውን ካርድ በመውሰዳቸው መደሰታቸውን ጠቁመው፣ ይበጀናል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።


 

ተማሪ ምናሉሽ አቱሞና ሰለሞን ኮያ በበኩላቸው በወሰዱት ካርድ ለሀገር ሰላምና ልማት ይበጃል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

ሌላው የቦንጋ ከተማ ነዋሪ አቶ አብዱልቃድር አደም በበኩላቸው፤ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም