ቀጥታ፡

ቦርዱ ለመራጮች ምዝገባ ያስቀመጠው ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት የምርጫ ካርድ እየወሰድን ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው ቀነ ገደብ መሠረት የመራጮች ምዝገባ ከመጠናቀቁ በፊት ዛሬ የምርጫ ካርዳችንን እየወሰድን ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ ሲሆን፤ እስከ ዛሬ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም የተራዘመው የጊዜ ገደብ በተለያየ ምክንያት ምርጫ ካርድ ያላወጡ ዜጎች እንዲመዘገቡ መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል።

ኢዜአ በመዲናዋ ተዘዋውሮ በምርጫ ጣቢያዎች ባደረገው ቅኝት የመጨረሻዋን ቀን በመጠቀም ዜጎች ካርድ እየወሰዱ መሆኑን ተመልክቷል።

በመዲናዋ በተለያዩ የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎች ተዘዋውሮ ካርዳቸውን ሲወስዱ ያገኛቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የምርጫ ካርድ ማውጣታችን ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀም ያስችለናል ብለዋል።

የምርጫ ካርድ ሲያወጣ ያገኘነው ዘሪሁን ፍቃዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመራጮች በቂ ጊዜ ለመስጠት የምዝገባ ጊዜውን በማራዘሙ ዛሬ የድምፅ መስጫ ካርድ መውሰዱን ተናግሯል፡፡

ማርሸት ጠንክር የተባለች አስተያየት ሰጪ በበኩሏ፤ የወሰደችውን የምርጫ ካርድ በመጠቀም ግንቦት 24 በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ይበጀኛል የምትለውን እጩ ለመምረጥ መዘጋጀቷን ገልጻለች፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የመዲናዋ ነዋሪ አቤል ኃይሉ በበኩሉ መምረጥ የሚያስችለኝን የመራጭነት ካርድ ወስጃለሁ ብሏል።

ግንቦት 24/2018 ዓ.ም  በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገርና በተለይም ለወጣቶች ተጠቃሚነት የተሻለ ፖሊሲ ያቀረበውን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቱን የተናገረው ደግሞ ካሳሁን ጉልማ የተባለ አስተያየት ሰጪ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም